የሙያ ማሕበራት ለመጀመሪያ ደረጃ የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት የላቀ ሚናቸውን ማጠናከር አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
የሙያ ማሕበራት ለመጀመሪያ ደረጃ የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት የላቀ ሚናቸውን ማጠናከር አለባቸው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 7/2018(ኢዜአ)፦የሙያ ማሕበራት ለመጀመሪያ ደረጃ የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት የላቀ ሚናቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ገለጹ፡፡
ከመጋቢት 6 እስከ 8 ቀን 2018 ዓ.ም የሚቆየው የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማህበር 37ኛ ዓመታዊ ኮንፍረንስ ማስጀመርያ መርሃ ግብር ተካሂዷል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ መንግሥት የጤና ስርዓቱን ለማዘመን በዘርፉ ከተሰማሩ ባለሙያዎችና ማህበራት ጋር በቅርበት እየሰራ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማህበር በመላው ኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችን በመክፈት ማህበረሰቡን በስፋት እያገለገለ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህም ምስጋና ይገባዋል ብለዋል፡፡
ማህበሩ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር በማከናወን ረገድ የሚጫወተው ሚና የላቀ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማህበር የጥናትና ምርምር ውጤቶች ለመንግሥት ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና ዕቅዶች ግብዓትነት ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው ብለዋል፡፡
የጥናትና ምርምር ውጤቶች የኢትዮጵያን አቅም በማሳየት ለዓለም አቀፉ የጤና አጠባበቅ ሥርዓት ገንቢ ሚና እየተወጣ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
መንግሥት የጤና ሥርዓቱን ለማዘመን በሚያደርገው ጥረት ማህበሩ ለጤና ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት እገዛ እያደረገ መሆኑን ገልጸው፤ ከኤች አይ ቪ/ኤድስ፣ የእናቶችና ህፃናት ጤና አጠባበቅ እና በቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ዙሪያ ወሳኝ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ማህበሩ የዜጎችን የጤና ፍላጎት፣ ጥራትና ተደራኝነት እንዲሁም ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በመጀመሪያ የጤና አገልግሎት አሃድ ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
የሙያ ማሕበራት መንግሥት የመጀመሪያ ደረጃ የጤና አገልግሎትን ጥራትና ተደራሽነት ለማሳደግ በሚያደርገው ጥረት ገንቢ ሚናቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማህበር ፕሬዝዳንት ዶክተር አጎናፍር ተካልኝ በበኩላቸው፤ ሁሉን አቀፍ የጤና ተደራሽነትን ማሳደግ የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ማህበሩ ከ10 ሺህ በላይ አባላት እንዳሉት ገልጸው፤ የባለሙያዎችን አቅም በመገንባትና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
37ኛው ዓመታዊ ኮንፍረንስ መንግስት የጤና ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚያደርገውን ጥረት መደገፍ ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ በጤና ተደራሽነት ዙሪያ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ያከናወኑ፣በጤናው ዘርፍ ንቁ ተሳትፎ ያደረጉ ግለሰቦችና ተቋማት እውቅና እና የሜዳልያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።