ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ተወዳዳሪነት የሚያጎለብት ምቹ ምኅዳር ተፈጥሯል-ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 7/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያን የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት የተወዳዳሪነት አቅምን የሚያጎለብት ምቹ ምኅዳር መፈጠሩን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር በመተባበር "ኢትዮጵያ - አዲሲቷ የኢንቨስትመንት መዳረሻ" በሚል መሪ ሃሳብ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።

በመድረኩ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ዮሐንስ መስፍን፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር)፣ የፌደራልና የክልል የኢንቨስትመንት ልማት ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

በዚሁ ጊዜ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)፤ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የሀገር ውስጥ ቀጣይነት ያለው ዕድገትን ለማሳለጥ ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።

በውጭ የኢንቨስትመንት መዕዋለ ነዋያቸውን ፈሰስ የሚያደርጉ ኩባንያዎች ከገንዘብ ባሻገር የዕውቀት፣ ክህሎትና ሰፊ የሥራ ዕድል በማምጣት ሀገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገትን እንደሚያፋጥን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ከናይጀሪያ በመቀጠል ብዙ ህዝብ የሚኖርባት ሁለተኛዋ የአፍሪካ ሀገር ናት፤ በከርሰ ምድርና ገጸ ምድር ሃብት የታደለችውን ዕምቅ ሃብትም በውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ማልማት ያስፈልጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስቀጠልም የውጭ ሃብት ፍሰትን በስፋትና ጥራት ማቅረብ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።


 

የኢትዮጵያን የብዝኅ ኢኮኖሚ ሥርዓት በኢንቨስትመንት ምኅዳሩ ላይ ከፍተኛ መነቃቃት በመፍጠር ጠንካራና ዘላቂ ልማትና ዕድገት እንዲመዘገብ እያስቻለ መሆኑን አንስተዋል።

የብዝኅ የኢኮኖሚ ሥርዓት ውጤታማነቱም ኢትዮጵያን የአፍሪካ ባለግዙፍ የኢኮኖሚ ባለቤት እያደረጋት እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ትግበራውም የግሉን ዘርፍ የኢኮኖሚ ተሳትፎ በማሳደግ በኢትዮጵያ የዕድገት ጉዞ የድርሻቸውን የሚወጡበት አስቻይ ሁኔታ መፍጠሩን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራም አስተማማኝ፣ ተገማችና የኢንቨስትመንትና የገበያ ከባቢን እየፈጠረ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት በወሳኝ ምዕራፍ መገኘትና የጂኦ-ፖለቲካዊ አመችነት የኢንቨስትመንት ስበትን በማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።

የመደመር መንግሥት ሰላማዊ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ከፍትሐዊ ባሻገር ኢትዮጵያ በቀጣናው የሚኖራትን የንግድና ኢንቨስትመንት ተወዳዳሪነት የበለጠ ለማሳደግ አቅም እንደሚኖረው ተናግረዋል።

በተጨማሪም አንጋፋው የኢትዮጵያ አየር መንገድም የኢትዮጵያን ምርቶች ለዓለም ገበያ በማቅረብ ወሳኝ ሚና እንዳለው አንስተዋል።

የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያም ነባርና አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ተጨማሪ ካፒታል የሚያገኙበትን ዕድል በመፍጠር እና የገበያ ትስስርን በማጠናከር ከፍተኛ የውጭ ሃብት ፍሰትን ለማጠናከር ጉለህ ጠቀሜታ እንዳለው አንስተዋል።

የኢትዮጵያን ምቹ የንግድና ኢንቨስትመንት ከባቢን የመፍጠር ወሳኝ የሪፎርም እርምጃዎች ስኬታማነት አጠናክሮ ለማስቀጠልም መገናኛ ብዙኅን የሚጠበቅባቸውን ከፍተኛ ኃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው አንስተዋል።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ፤ ኢዜአ ካለፉት ሰማኒያ አራት ዓመታት አንስቶ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ሀገራዊ መግባባት የአጀንዳ ጉዳዮች ዙሪያ በሀገር ውስጥና በውጭ ቋንቋዎች በትኩረት እየሰራ የሚገኝ ተቋም ነው ብለዋል።

በውጭ በእንግሊዝኛ፣ አረብኛና ፈረንሳይኛ እንዲሁም በአምስት የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች መረጃዎችን በማሰባሰብ ለሕብረ ብሔራዊ አንድነትና ሀገራዊ መግባባት ዜናና ዜና ነክ ጉዳዮች ላይ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በዜናና ዜና ነክ ጉዳዮች የሚሰሩ ዘገባዎችም ከኢዜአ የመረጃ ማሰራጫ ዘዴዎች በተጨማሪ ለሀገር ውስጥና ለበርካታ የውጭ መገናኝ ብዙኅን መረጃን በማመንጨት እያዳረሰ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር በመተባበር የኢትዮጵያን ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻነት ለማስተዋወቅ "ኢትዮጵያ - አዲሲቷ የኢንቨስትመንት መዳረሻ" በሚል መሪ ሃሳብ የምክክር መድረክ መዘጋጀቱን አንስተዋል።

መድረኩም የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት ምኅዳር በማስፋት የተገኙ ውጤቶችንና ቀጣይ ትልሞችን በማስተዋወቅ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው አንስተዋል።

#Ethiopian_News_Agency

#ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም