ቀጥታ፡

በዞኖቹ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ተስፋ ሰጪ ውጤት እየተመዘገበ ነው

አምቦ/ጭሮ መጋቢት 7/2018 (ኢዜአ):- በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ሸዋ እና ምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑ ተገለጸ።

በምዕራብ ሸዋ ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት የመስኖ ኤክስቴንሽን ባለሙያ አቶ ቢቂላ ጉቱ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በዞኑ በዘንድሮው የበጋ ወቅት 408 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ ወደ ሥራ የተገባ ሲሆን እስካሁን ከ388 ሺህ ሄክታር በላይ በዘር ተሸፍኗል።

በዘር ከተሸፈነው መሬት ውስጥ  በ21 ወረዳዎች ከ147 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በኩታ ገጠም እየለማ ሲሆን ከዚህም 15 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።

ለአርሶ አደሩ ግብዓት የማቅረብ፣አረም የማስወገድ እና የተባይ መከላከል ሥራዎች የባለሙያዎች ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተመሳሳይም በምዕራብ ሐረርጌ ዞን በ15 ወረዳዎች ውስጥ ከ58 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ እየለማ መሆኑን የዞኑ ግብርና እና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።


 

በፅህፈት ቤቱ የስንዴ ልማት አስተባባሪ አቶ ሀቢብ አብዱልከሪም በልማት ስራው ከ97 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ ሲሆን  2 ሺህ የሚጠጉ የውኃ መሳቢያ ሞተሮች ተከፋፍለዋል ብለዋል።

በዞኑ በአጠቃላይ 3 ሚሊዮን ኩንታል ገደማ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል ነው ያሉት።

በምዕራብ ሸዋ ዞን በኢሉ ገላን ወረዳ በልማቱ የተሰማሩ አርሶ አደሮች እንደሚሉት፣ ከግብርና ባለሙያዎች በሚያገኙት ምክር በመታገዝ ለማሳቸው ተገቢውን እንክብካቤ እያደረጉ ነው።

አርሶ አደር ብርሃኑ ልኩማ "በቂ ማዳበሪያና የተሻሻለ ዝርያ በመጠቀሜ የተሻለ ምርት አገኛለሁ ብዬ እጠብቃለሁ፤ ይህም ኑሮዬን ለማሻሻል ይረዳኛል" ብለዋል።

ሌላው አርሶ አደር ገዛኸኝ ደረሰ፣ ቀደም ሲል በክረምት ብቻ ይታረስ የነበረውን ልምድ በመቀየር፣ አሁን በመስኖ በማልማታቸው የገቢያቸው መጠን በእጥፍ እንደሚያድግ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

አርሶ አደሮቹ ከአንድ ሄክታር መሬት ከ25 እስከ 30 ኩንታል ምርት ለማግኘት አቅደው እየሠሩ ይገኛሉ።


 

የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ጡሎ ወረዳ የኢፋ አንዶዴ ቀበሌ አርሶ አደር ሲራጅ ዓሊ፣ በሞተር በመታገዝ በዓመት ሁለት ጊዜ ማምረት መጀመራቸውን ገልጸው፣ ከልማቱ የሚያገኙት ገቢ ማዳበሪያ ለመግዛትና ሥራቸውን ለማስፋፋት እንደረዳቸው ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም