የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ይበልጥ ለማረጋገጥ የሙያ ማህበራት ሚና የላቀ ነው - ዶክተር ደረጄ ዱጉማ - ኢዜአ አማርኛ
የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ይበልጥ ለማረጋገጥ የሙያ ማህበራት ሚና የላቀ ነው - ዶክተር ደረጄ ዱጉማ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 6/2018(ኢዜአ)፦መንግስት የጤና አገልግሎት ጥራትንና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በሚያደርገው ጥረት የሙያ ማህበራት የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ ገለፁ።
የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማህበር ከመጋቢት 6 እስከ 8 ቀን 2018 ዓ.ም የሚቆየውን 37ኛ ዓመታዊ ኮንፍረንስ ማስጀመርያ መርሃ ግብር አካሂዷል።
በመክፈቻ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት ዶክተር ደረጄ ዱጉማ ባስተላለፉት መልዕክት መንግስት የጤና ስርዓቱን ለማጠናከር በዘርፉ ከተሰማሩ የሙያ ማህበራት ጋር በቅርበት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማህበር በመላው ሀገሪቱ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶችን በመክፈት ማህበረሰቡን በስፋት እያገለገለ መሆኑ የሚመሰገን ነው ብለዋል።
ማህበሩ ለጤና ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠትና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር በማከናወን ረገድ የሚጫወተው ሚና የላቀ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማህበር ፕሬዝዳንት ዶክተር አጎናፍር ተካልኝ በበኩላቸው ማህበሩ ሁሉን አቀፍ የጤና ተደራሽነትን ለማሳደግ የሚከናወኑ ተግባራት ውጤታማ እንዲሆኑ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ማህበሩ ከ10 ሺህ በላይ አባላት ያሉት ሲሆን የባለሙያዎችን አቅም በመገንባትና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም 37ኛው ዓመታዊ ኮንፍረንስ መንግስት የጤና ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚሰራቸውን ስራዎች በጋራ በመደገፍ ላይ ያተኮረ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።
ዓመታዊ ኮንፍረንሱ ከመጋቢት 6 እስከ 8 ቀን 2018 ዓ.ም በተለያዩ ሁነቶች እንደሚከናወን ተጠቅሷል፡፡
በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ በጤና ተደራሽነት ዙሪያ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ላከናወኑ፣ በተለያዩ የጤና ዘርፍ እንቅስቃሴዎች ንቁ ተሳትፎ ላደረጉ ግለሰቦችና ተቋማት እውቅና እና የሜዳልያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ