ለመቄዶንያ የሚደረግ ድጋፍ የመንፈስ ብርታትንና በረከትን ያስገኛል - ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ - ኢዜአ አማርኛ
ለመቄዶንያ የሚደረግ ድጋፍ የመንፈስ ብርታትንና በረከትን ያስገኛል - ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 6/2018 (ኢዜአ)፡- ለመቄዶንያ የሚደረግ ድጋፍ የመንፈስ ብርታትንና በረከትን የሚያስገኝ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ እንዲያደርጉ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ጥሪ አቀረቡ።
ፕሬዚዳንቱ የመቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ-ግብርን አስጀምረዋል።
በዚሁ ወቅትም፤ ማኅበራዊ ኃላፊነት ለመንግሥት ብቻ የሚተው ተግባር አለመሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል።
በመቄዶንያ ማዕከል ውስጥ ተስፋ መቁረጥና ማጣት ሲሸነፍ መመልከታቸውን ጠቅሰው፤ ማዕከሉ ለተጨነቁ ወገኖች ተስፋ የለመለመበት የርኅራሄ ሥፍራ መሆኑን ተናግረዋል።
የሕይወት ምሉዕነት የሚረጋገጠው ካለው ላይ ቆርሶ በመስጠት ነው፤ ለተቸገሩ መድረስና ለወገን መቆም ትልቅ የመንፈስ እርካታን የሚሰጥ ተግባር ነው ሲሉም አስገንዝበዋል።
መረዳዳትና መደጋገፍ የኢትዮጵያውያን ጥንታዊ ባህል መሆኑንና መቄዶንያ ይህን ዕሴት በተደራጀና ሥርዓት ባለው መልኩ እየተገበረ መሆኑንም አመላክተዋል።
መንግሥት ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
ማዕከሉ እያከናወነ ያለው የበጎ አድራጎት ተግባር የብዙዎችን ልብ የጠገነና ለትውልድ በጎነትን የሚያሰርፅ ሥራ መሆኑንም አንስተዋል።
ለመቄዶንያ የሚደረግ ድጋፍ የመንፈስ ብርታትንና በረከትን የሚያስገኝ በመሆኑ፤ መላው ኢትዮጵያውያን በገቢ ማሰባሰቢያው ላይ በንቃት እንዲሳተፉም ጥሪ አቅርበዋል።