ቀጥታ፡

ለ2018 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የላቀ ሀገራዊ ራዕይን በሚያሳካ መልኩ ዝግጅት እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ፤መጋቢት 6/2018 (ኢዜአ)፡-ለ2018 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የላቀ ሀገራዊ ራዕይን በሚያሳካ መልኩ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡ 

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት የተጀመረ ሲሆን፤ መርሃ ግብሩ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክሏል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም መሪ ሥራ አስፈፃሚ ፋኖሴ መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ለዘንድሮው መርሃ ግብር የመጀመሪያ ዙር የችግኝ ዝግጅት ተጠናቋል። 

ለስኬታማነቱም በርካታ ቁልፍ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመው፤ ሰባት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኞችን  ለመትከል የሚያስችል ዕቅድ መዘጋጀቱን አብራርተዋል። 

በዚህም እስካሁን ከስድስት ቢሊዮን በላይ ችግኞች እየተዘጋጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡  

ከችግኞቹ መካከልም 40 በመቶው ሀገር በቀል የደን ችግኞች ሲሆኑ፤ ቀሪው 60 በመቶው ደግሞ እንደ ፍራፍሬ እና የእንስሳት መኖ ያሉ ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው ናቸው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በሀገር አቀፍ ደረጃ 110 ሺህ የችግኝ ጣቢያዎች ወደ ሥራ መግባታቸውን ጠቁመዋል፡፡ 

የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ መሆኑ ጠቅሰው፤ ከሰባት  ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆን የመሬት ይዞታ በዲጂታል ጂኦ-ሪፈረንስ ክትትል የሚደረግበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በተለይም በአንድ ጀምበር በሚከናወነው ተከላ ላይ የቴክኖሎጂው አጠቃቀም ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል፡፡ 

መርሃ ግብሩ በርካታ ትልልቅ ግቦችን ያነገበ ሲሆን፤ የአየር ንብረት ለውጥን መከላከል፣ የምግብ ዋስትና፤ ኢኮኖሚና ቀጣናዊ ትስስርን ማጠናከር ዋነኞቹ ናቸው ብለዋል፡፡ 

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ብቻ ሳይሆን የሥራ ዕድል ፈጠራን፣ የተፋሰስ ልማትን እና የአፈርና ውሃ ጥበቃን ያካተተ ሁለንተናዊ የልማት ስትራቴጂ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም