ቀጥታ፡

ማንችስተር ዩናይትድ ከአስቶንቪላ የሚያደርጉት የሊግ ጨዋታ ተጠባቂ ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 6/2018 (ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 30ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

በኦልድትራፎርድ ስታዲየም ማንችስተር ዩናይትድ ከአስቶንቪላ ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።



ማንችስተር ዩናይትድ በ51 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል። አስቶንቪላ በተመሳሳይ 51 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጦ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በማይክል ካሪክ የሚመራው ማንችስተር ዩናይትድ በ29ኛ ሳምንት በኒውካስትል ዩናይትድ የ2 ለ 1 ሽንፈት አስተናግዷል።

ውጤቱ ዩናይትድ በካሪክ ስር ያስተናገደው የመጀመሪያ የሊግ ሽንፈት ነው።

ተጋጣሚው አስቶንቪላ ባለፉት ሁለት የሊግ ጨዋታዎች በቼልሲ እና ዎልቭስ ሽንፈት አስተናግዷል።

ጨዋታው በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ ለማድረግ ለሚፎካካሩት ክለቦች ወሳኝ የሚባል ነው።

የ47 ዓመቱ አንቶኒ ቴይለር ተጠባቂውን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።



በሌላኛው መርሐ-ግብር ሊቨርፑል ከቶተንሃም ሆትስፐርስ ምሽት 1 ሰዓት ከ30 ላይ በአንፊልድ ሮድ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ሊቨርፑል በ48 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል። ቀያዮቹ በ29ኛ ሳምንት በዎልቭስ ያልተጠበቀ የ2 ለ 1 ሽንፈት ማስተናገዳቸው የሚታወስ ነው።

ቶተንሃም ሆትስፐርስ በ29 ነጥብ 16ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

በውጤት ማጣት ቀውስ ውስጥ የሚገኘው ቶተንሃም ሆትስፐርስ ባለፉት 11 የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም።

ጨዋታው ለወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ሊቨርፑል በሻምፒዮንስ ሊግ ለመሳተፍ በሚያደርገው ጉዞ ወሳኝ ነው።

የመውረድ ስጋት ያንዣበበት ቶተንሃም ሶስት ነጥብ መጠነኛ የሆነ እፎይታ ይሰጠዋል።

 

ክሪስታል ፓላስ ከሊድስ ዩናይትድ እና ኖቲንግሃም ፎረስት ከፉልሃም በተመሳሳይ ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም