በተጠባቂው ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሃዋሳ ከተማን አሸነፈ - ኢዜአ አማርኛ
በተጠባቂው ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሃዋሳ ከተማን አሸነፈ
አዲስ አበባ ፤ መጋቢት 5 /2018 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ24ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሃዋሳ ከተማን 4 ለ 2 አሸንፏል።
ማምሻውን በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ናትናኤል ዳንኤል፣ ሁዘይፋ ሻፊ እና ዩጋንዳዊው ሳይመን ፒተር በጨዋታ፣ አዲስ ግደይ በፍጹም ቅጣት ምት የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል።
ጌታነህ ከበደ እና ሽመልስ በቀለ ለሃዋሳ ከተማ ጎሎቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
በሊጉ ሰባተኛ ድሉን ያስመዘገበው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ30 ነጥብ ደረጃውን ከ13ኛ ወደ 10ኛ ከፍ አድርጓል።
በውድድር ዓመቱ ስድስተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ሃዋሳ ከተማ በበኩሉ በ40 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።
ሃዋሳ ከተማ ከሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት የማጥበብ እድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የፊት መስመር ተሰላፊ አዲስ ግደይ በሊጉ ያስቆጠራቸውን ግቦች ብዛት ወደ 10 ከፍ በማድረግ ተመሳሳይ ግብ ካስቆጠረው የሲዳማ ቡናው አቤል ያለው ጋር የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን በጋራ መምራት ችሏል።
በሌላኛው መርሐ-ግብር ኢትዮጵያ ቡና አዳማ ከተማን 3 ለ 2 አሸንፏል።
በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው ጨዋታ ዘላለም አባተ፣ በፍቃዱ አለማየሁ እና ሀምዛ ሱልጣን ለቡናማዎቹ ጎሎችን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
አሕመድ ሁሴን ለአዳማ ከተማ ግቦቹን አስቆጥሯል።
በሊጉ ዘጠነኛ ድሉን ያሳካው ኢትዮጵያ ቡና አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ32 ነጥብ ደረጃውን ከ10ኛ ወደ 8ኛ ከፍ አድርጓል።
በአንጻሩ በሊጉ አምስተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው አዳማ ከተማ በ33 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃን ይዟል። ቡድኑ ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች አላሸነፈም።
ቀን ላይ በተደረጉ የ24ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ኢትዮጵያ መድን አርባምንጭ ከተማን 2 ለ 0፣ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ድሬዳዋ ከተማን 1 ለ 0 አሸንፈዋል።