ቀጥታ፡

በመዲናዋ በህገ ወጥ የነዳጅ ግብይት የተሰማሩ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናከሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 5/2018(ኢዜአ)፦ በመዲናዋ በህገ ወጥ የነዳጅ ግብይት በተሰማሩ አካላት ላይ የሚወሰደው ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ ተጠናከሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ ገለጹ።

የአስተዳደሩ ንግድ ቢሮ ከነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ጋር በመተባበር በከተማዋ ከነዳጅ ግብይት ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን ለመቅረፍ ከዘርፉ ተዋናዮች ጋር ውይይት አካሂዷል።


 

በዚሁ ወቅት የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ፤ የኢትዮጵያን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማሳለጥ የነዳጅ ምርት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።

ለዚህም መንግስት የነዳጅ ምርትን በከፍተኛ የገንዘብ ድጎማ ለተጠቃሚው ማህበረሰብ እንዲሰራጭ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ሆኖም አንድ አንድ ማደያዎችና አከፋፋይ ኩባንያዎች የነዳጅ ምርትን በሕጋዊ ሥርዓት እንዳይሰራጭ በማድረግ ሕገ-ወጥ ተግባር እንደሚፈጽሙ አንስተዋል።

በአዲስ አበባም በቂ የነዳጅ ክምችት እያለ ከአሰራር ውጪ ደንበኞችን በማጉላላት ሕገ-ወጥ ተግባር የሚፈጽሙ አካላት መኖራቸውን አስረድተዋል።

በቀጣይም የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ በማጠናከር የአሰራር ጥሰት የሚፈጽሙ አካላት ላይ ጠንካራ ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድ አሳስበዋል።


 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ኃላፊ ሀቢባ ሲራጅ በበኩላቸው፤ በነዳጅ የምርት ሥርጭት ወቅት ሕገ-ወጥ የግብይት ድርጊቶች እንደሚስተዋሉ በተደረገ ክትትልና ቁጥጥር ተረጋግጧል ብለዋል።

መድረኩ በነዳጅ ምርት ሥርጭት ወቅት ከተቀመጠው ሕጋዊ የአሰራር ውጪ ሕገ-ወጥ ግብይት የሚፈጽሙ ማደያዎችንና ኩባንያዎችን ለማረም ጉልህ ጠቀሜታ እንዳለው አስረድተዋል።

በቀጣይም በግብይቱ ላይ የሚስተዋሉ ሕገ-ወጥነቶችን በማረም የሚወሰደው ሕግና ሥርዓትን የማስከበር ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ደስታው መኳንንት (ዶ/ር)፤ መንግስት በከፍተኛ የገንዘብ ድጎማ ወደሀገር ቤት የሚያስገባውን የነዳጅ ምርት በሕጋዊ ሥረዓት ማሰራጨት ያስፈልጋል ብለዋል።

የነዳጅ ምርት የሚያሰራጩ ማደያዎችና አከፋፋዮችም በተቀመጡ የአሰራር ሥርዓት መሠረት ለተጠቃሚው ማዳረስ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ በበኩላቸው፤ በነዳጅ ምርት ሥርጭት ላይ የሚስተዋሉ ሕገ-ወጥነቶች ለማረም ጠንካራ እምርጃ ይወሰዳል ብለዋል።

ባለድርሻ አካላትም በወሰዱት ኃላፊነት መሰረት የነዳጅ ምርትን ሕጋዊ የአሰራር ሥርዓት ተከትለው ማሰራጨትና ማከፋፈል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም