የ"ፊቼ ጫምበላላ" በዓል እሴቶች ለህዝቦች አንድነትና ትስስር መጠናከር የጎላ ሚና አላቸው - ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ - ኢዜአ አማርኛ
የ"ፊቼ ጫምበላላ" በዓል እሴቶች ለህዝቦች አንድነትና ትስስር መጠናከር የጎላ ሚና አላቸው - ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ
ሀዋሳ፤ መጋቢት 5/2018(ኢዜአ)፦ የሲዳማ የዘመን መለወጫ "ፊቼ ጫምበላላ" በዓል የአብሮነት፣ የፍቅርና የሰላም እሴቶች ለህዝቦች አንድነትና ትስስር መጠናከር የጎላ ሚና እንዳለው ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።
በፊቼ ጫምባላላ በዓል ዋዜማ የ"ፊጣራ" ሥነ ስርዓት በሀዋሳ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተካሄደ ነው።
በሥነ-ስርዓቱ ላይ የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) እና የሲዳማ ክልል ዋና አፈ ጉባኤ ፋንታዬ ከበደን ጨምሮ ሌሎች የፌዴራልና የክልል የሥራ ኃላፊዎችና ተጋባዥ እንግዶች ታድመዋል።
በሥነ-ስርአቱ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ፤ የሲዳማ የአዲስ ዘመን መለወጫ "የፊቼ ጫምባላላ" በዓል የሠላም፣ የፍቅርና የአብሮነት በዓል መሆኑን ተናግረዋል።
ያለፈው አሮጌ ዓመት ተሸኝቶ አዲስ ዓመት በአዲስ ተስፋ የምንቀበልበት ልዩ በዓል ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ፊቼ ጫምበላላ የተጣሉ የሚታረቁበት፣ ያዘኑ የሚጽናኑበት፣ አቅም የሌላቸው የሚደገፉበትና ሰብአዊነት ጎልቶ የሚታይበት የደስታ በዓል መሆኑንም ነው ያመለከቱት።
በዓሉ የያዛቸው እሴቶች ለህዝቦች ጠንካራ አንድነትና ትስስር የጎላ ሚና ስላላቸው አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
በዓሉ ያለፈው ዓመት የሥራ ውጤቶችን በመፈተሽ ጠንካራ ጎኖችን የሚጠናከሩበትና ደካማ ጎኖች እርምት የሚወሰድባቸው በመሆኑ የስራ ባህልን ያጠናክራል።
በአዲስ ዓመት የላቀ ስኬት ለማስመዝገብ በተስፋ የምንሻገርበት በዓል ነው ያሉት አቶ ደስታ፣ ህብረተሰቡም አንድነትና ሰላሙን በማስቀጠል ለላቀ ስኬት እንዲተጋ አስገንዝበዋል።
የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ጃጎ አገኘሁ በበኩላቸው ፊቼ ጫምባላላ የሲዳማ የአዲስ ዘመን ብስራት መሆኑን ተናግረዋል።
የሲዳማ አያንቱዎች የሥነ ክዋክብት እንቅስቃሴን ተከትለው የሚውልበትን ዘመንና ቀኑን እንደሚወስኑ ተናግረው ይህም አባቶች ያላቸው ዘመናትን የተሻገረ ጥልቅ ዕውቀት ያሳያል ብለዋል።
በዓሉ ቂምና ቁርሾ ተፈትቶ በይቅርታ፣ በምህረትና በአዲስ ተስፋ የሚሻገሩት መሆኑን ገልጸው ይህም በህብረተሰቡ መካከል ጠንካራ አንድነትና ትስስር ለመፍጠር ያለውን ከፍተኛ አቅም ያመላክታል ነው ያሉት።
በመድረኩ ከሥራ ኃላፊዎች በተጨማሪ ከአጎራባች ክልሎችና ዞኖች የመጡ እንግዶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ሌሎች ታዋቂ ግለሰቦችና ተጋባዥ እንግዶች ታድመዋል።