ተመራቂዎች በሰለጠኑበት የሙያ መስክ ማሕበረሰቡንና ሀገራቸውን በትጋት ማገልገል ይገባቸዋል-የአምቦ ዩኒቨርሲቲ - ኢዜአ አማርኛ
ተመራቂዎች በሰለጠኑበት የሙያ መስክ ማሕበረሰቡንና ሀገራቸውን በትጋት ማገልገል ይገባቸዋል-የአምቦ ዩኒቨርሲቲ
አምቦ፤መጋቢት 5/2018 (ኢዜአ)፦ ተመራቂ በሰለጠኑበት የሙያ መስክ ማሕበረሰቡንና ሀገራቸውን በትጋት ማገልገል እንደሚገባቸው የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ባይሳ ለታ (ዶ/ር) ተናገሩ ።
የአምቦ ዩኒቨርሲቲ በተለያየ የትምህርት መስክ ያሰለጠናቸውን 2 ሺህ 260 ተማሪዎችን አስመርቋል።
የዪኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ባይሳ ለታ ( ዶ/ር ) በምርቃቱ ስነ-ስርዓት ላይ እንደተናገሩት፤ ተመራቂ ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲው በቀሰሙት ልምድ ቤተሰባቸውን፣ሀገራቸውን እና ማሕበረሰቡን በታማኝነት ለማገልገል ከወዲሁ መዘጋጀት ይገባቸዋል።
በዋናነትም ጊዜያቸውን በአግባቡ በመጠቀም የወገኖቻቸውን እና የሀገራቸውን የልማት ፍላጎትን ለማሳካት እንዲችሉም ከወዲሁ እራሳቸውን ማዘጋጀት እንዳለባቸውም ነው የተናገሩት።
በተጨማሪም ተማሪዎቹ በትምህርት ላይ ባገኙት እውቀት እና ክህሎት ለሃገራቸው እና ለማህበረሰባቸው ፍትሃዊ የሆነ አገልግሎት እንደሚገባቸውም ነው የተናገሩት።
ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ስራው በተጨማሪ የምርምርና የማኀበረሰብ አገልግሎትን ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም ነው ያመለከቱት።
ከተመራቂ ተማሪዎች መካከል በኢኮኖሚክስ ትምህርት ከፍተኛ ውጤት በማምጣት የዋንጫ ተሸላሚ የሆነው ኬናዋቅ ትርፌሳ እንደሚለው ወጣቱ የዓላማ ጽናት ካለው ያሰበው ደረጃ ለመድረስ የሚያግደው እንደሌለ ተገንዝቦ መስራት አለበት።
''ጊዜዬን በአግባቡ በመጠቀመም በምወደው የሙያ ዘርፍ በከፍተኛ ማዕረግ በመመረቄ ልዩ ደስታ ፈጥሮብኛል'' ያለው ተመራቂው፣ በዚሁ መሰረት ሀገርና ሕዝብ በማገልገል የሚጠብቅብኝን ኃላፊነት ለመወጣት ተዘጋጅቼያለሁ ነው ያለው።
በግብርና ኢኮኖሚ ትምህርትም እንዲሁ ከፍተኛ ውጤት በማምጣት የሜዳሊያ ተሸላሚ የሆነው ጋዲሳ ታከለ በበኩሉ፤ በዩኒቨርሲቲ ቆይታው የቀሰመውን ልምድ ህዝቡን በቁርጠኝነት ለማገልገል እንደሚያውለው ነው ያረጋገጠው።
ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት ከ19 ሺህ በላይ ሚሆኑ ተማሪዎችን ከመጀመሪያ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ በተለያዩ መርሃ ግብሮች እያሰለጠነ መሆኑም በዚሁ ወቅት ተገልጿል።