ቀጥታ፡

ሰላምን ከማጽናት ጎን ለጎን የወጣቱን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው- የባህርዳር ከተማ አስተዳደር

ባህርዳር፤ መጋቢት 5/2018(ኢዜአ)፡-ሰላምን ከማጽናት ጎን ለጎን የተጠናከረ የልማት ስራ በመስራት የወጣቱን ተሳትፎና ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው ገለፁ።

የባህርዳር ከተማ አስተዳደር የስራ ዕድል ተጠቃሚ ከሆኑ ወጣቶች ጋር በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ እያካሔደ ነው። 


 

‎የአስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ ‎የሀገር አንድነትና ብልፅግናን በማረጋገጥ ጠንካራ ሃገር መገንባት የሚቻለው ወጣቱን ትውልድ በንቃት በማሳተፍና ዘላቂ ተጠቃሚነቱን ማረጋገጥ ሲቻል ነው። 

በአሁኑ ወቅትም ‎ወጣቱ ትውልድን የሰላምና የልማት ዋና አቅም አድርጎ በመሰራቱ ስኬታማ ስራዎችን ለማከናወን እንደተቻለም ነው የገለጹት።

ከተማ አስተዳደሩም በኮሪደርና ሌሎች ሰፋፊ የልማት ፕሮጀክቶች ትግበራና በተለያዩ የሙያ መስኮች  ወጣቱ የስራ እድል እንዲያገኝና የልማት አርበኝነቱን እንዲያረጋግጥ እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

ይሕንኑ ተሞክሮ ‎በማስፋትም የስራ ዕድል ተጠቃሚ ያልሆኑ ወጣቶችን በማደራጀት፣ በማሰልጠን፣የብድርና የመስሪያ ቦታ ድጋፎችን በማድረግ ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉን ጠቅሰዋል።

‎የከተማ የአስተዳደሩ ስራና ስልጠና መምሪያ ኃላፊ አቶ ዘመነ አሰፋ በዚሁ ወቅት ባቀረቡት ጽሁፍ እንደገለጹት፤ በከተማዋ በበጀት ዓመቱ ለ45 ሺህ 349 ወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር ግብ ተይዞ እየተሰራ ይገኛል።

‎ባለፉት 8 ወራትም በግብርና፤ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኮንስትራክሽን፣ በኮሪደር ልማትና ሌሎች ዘርፎች ለ38 ሺህ 546 ወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር መቻሉን ገልፀዋል።

‎የአማራ ክልል ወጣቶች ማህበር ፕሬዝዳንት ወጣት ጋሻው አዘነ በበኩሉ፤ ስላምን አፅንቶ በማዝለቅና ልማቱን በማፋጠን አገራችን ወደ ብልጽግና ማማ ለማሸጋገር የወጣቱ ሚና የላቀ መሆኑን ነው የሚናገረው።

‎የወጣቱን ተጠቃሚነት በዘላቂነት ማረጋገጥ የሚቻለው በየደረጃው ሰላምን ማስፈን ሲቻል መሆኑን በመገንዘብም ወጣቱ ሰላምን ለማጽናት ተግቶ አንደሚሰራ ነው ያመለከተው።

‎የመድረኩ ተሳታፊ ነፃነት አጠቃ በበኩሏ ያለ ሰላም ሰርቶ መለወጥም ለአገር እድገት ማምጣት የማይታሰብ በመሆኑ የተገኝውን ሰላም ለማጽናት በትኩረት እንሰራለን ነው የምትለው።

‎በውይይት መድረኩ ላይም ከሁሉም ክፍለ ከተሞችና ቀበሌዎች የተውጣጡ ወጣቶችና የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም