በጋሞ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ በማሰባሰብ የበኩላችንን እንወጣለን - አርቲስቶች - ኢዜአ አማርኛ
በጋሞ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ በማሰባሰብ የበኩላችንን እንወጣለን - አርቲስቶች
አርባ ምንጭ፤ መጋቢት 5/2018 (ኢዜአ)፡-በጋሞ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ በማሰባሰብ የበኩላቸውን እንደሚወጡ አርቲስቶች ገለጹ።
የተለያዩ አርቲስቶች በጋሞ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ወገኖችን በስፍራው ተገኝተው አጽናንተዋል።
አርቲስት ታምሩ ብርሃኑ በዚሁ ወቅት እንደተናገረው፤ በጋሞ ዞን በተከሰተው አደጋ የተጎዱ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋም ድጋፍ በማሰባሰብ ሂደት ውስጥ የድርሻውን እንደሚወጣ ተናግሯል።
በአደጋው በሰው ህይወትና በንብረት ላይ በደረሰው ጉዳት ማዘኑን ገልጾ አርቲስት የህዝብ ልጅ እንደመሆኑ መጠን ይህን ጊዜ በመተባበርና በመተጋገዝ እናልፈዋለን ብሏል፡፡
አርቲስት ተስፋዬ ሲማ በበኩሉ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ በማሰባሰቡ ሒደት አርቲስቶች የድርሻችንን ሚና ለመወጣት እንሰራለን ነው ያለው።
ለወገን ደራሽ ወገን በመሆኑ የተለያዩ አካላትን በማስተባበር ለተጎጂዎች ድጋፍ ለማሰባሰብ የበኩሉን እንደሚወጣ አመልክቷል።
አርቲስት ፀደኒያ ገብረማርቆስ እና አርቲስት ዘለቀ ገሠሠ በበኩላቸው፤ በጋሞ ዞን የተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ባስከተለው ጉዳት ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማቸው ገልጸዋል።
ጉዳቱ እጅግ አሳዛኝ በመሆኑ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችና ባለሀብቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ያቀረቡት አርቲስቶቹ በሀገር ውስጥም በውጭም ድጋፍ ለማሰባሰብ በሚደረግ ሂደት የሚጠበቅብንን እንወጣለን ሲሉም ቁርጠኝነታቸውን አረጋግጠዋል።