ምርጫው ፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የበኩላችንን እንወጣለን - የወሎ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ - ኢዜአ አማርኛ
ምርጫው ፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የበኩላችንን እንወጣለን - የወሎ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 5/2018(ኢዜአ)፦ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የበኩላችንን እንወጣለን ሲል የወሎ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ገለጸ።
ፓርቲው ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዝግጅቱን ማጠናቀቁንም አስታውቋል።
የወሎ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(ወዴፓ) የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የማኒፌስቶ እና የምርጫ ምልክት ይፋ ማድረጊያ መርሃ ግብር አካሂዷል፡፡
ፓርቲው በመርሃ ግብሩ እጬዎችን የማስተዋወቅና ለምርጫው እያደረጉት ያለውን ዝግጅት አስተዋውቋል።
በዚህም የወሎ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የመወዳደሪያ ምልክት ቁልፍ መሆኑን ይፋ ያደረገ ሲሆን፤ ፓርቲው የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ"ከውሀ ወደ ውሀ" በሚል መሪ መልዕክት መሰየሙን ገልጿል፡፡
የፓርቲው ፕሬዚዳንት ነፃነት ጣሰው በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የወሎ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(ወዴፓ) የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍትሐዊ እና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን የበኩሉን ይወጣል ብለዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እንደተሳካ ሁሉ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄን ምላሽ ለማስገኘት በሚደረገው ጥረት የበኩሉን እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።
ስለሆነም የወሎ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ በነቃ ተሳትፎ ከመንግሥት ጎን ለመቆም ዝግጁ መሆኑን አብራርተዋል፡፡