ቀጥታ፡

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ማህበራዊ ኃላፊነቱን የመወጣት ተግባሩን አጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 5/2018(ኢዜአ)፦የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ማህበራዊ ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት የሚያስችለውን ተግባራትን  አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ።

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ለመቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል የማዕድ ማጋራትና የአምስት ሚሊየን ብር የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ ተቋሙ ማህበራዊ ኃላፊነትን በአግባቡ መወጣት የሚያስችሉ በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል።


 

ባለፋት ሁለት ዓመታት ተቋሙ ባደረገው ሪፎርም ማህበራዊ ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት የሚያስችሉ ስራዎችን ለማከናወን በሚያስችል መልኩ በፖሊሲ ደረጃ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተቋሙና በተለያዩ አካባቢ ለሚገኙ አረጋዊያን እንዲሁም ለተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ ሲያረግ መቆየቱን ገልጸዋል።

ተቋማት በሚገኙት አካባቢ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት የሚያስችላቸውን ተግባራት መወጣት እንዲችሉ በሪፎርማቸው ውስጥ ይህን ታሳቢ ማድረግ እንደሚገባቸው ገልጸው፤ በዚህም ሀገር ውስጥ ያሉ  ችግሮችን  በጋራ መፍታት እንደሚቻል ተናግረዋል።

መቄዶንያ የአረጋውያን እና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል በርካታ ጧሪ ቀባሪ የሌላቸው ዜጎች ከጎዳና ላይ በማንሳት የሚንከባከብ የአገር በለውለታ ተቋም መሆኑን ተናግረዋል።

ስለሆነም ተቋሙን ማገዝና መደገፍ ውዴታ ብቻ ሳይሆን በሰብዓዊነት ሊተገበር የሚገባ ግዴታ መሆኑን ጠቅሰው፤ በግልና በተቋም ድጋፍ  እየተደረገ ነው ብለዋል።

በዚህም በዛሬው ዕለት የማዕድ ማጋራት እና የአምስት ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፋ በተቋሙ መደረጉን ገልጸዋል።

በቀጣይም ድጋፋን  በቋሚነት ማደረግ የሚያስችሉ አሰራሮችን እንደሚዘረጋ ተናግረዋል።

የመቄዶኒያ የአረጋውያን እና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል መስራች እና ሥራ አስኪያጅ ቢኒያም በለጠ በበኩሉ፤ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ድጋፎችን ሲያደርግ  መቆየቱን ገልጿል።

''አረጋዊያንን መደገፍ ከፈጣሪ ትልቅ ዋጋ የሚያስጥ እና የህሊና እረፍት የሚሰጥ ነው'' በመሆኑን ዛሬ የተደረገው የገንዘብ ድጋፍ ተቋሙ የጀመራቸውን ትላልቅ ስራዎች ለማስፈጸም ትልቅ አቅም እንደሚሆን ገልጸዋል።

ለተደረገው የማዕድ ማጋራት እና የገንዝብ ደጋፍ በማዕከሉ በሚገኙ አረጋዊያን እና ህሙማን ስም  ምስጋና አቅርበዋል።

                                                                                   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም