ቀጥታ፡

በክልሉ ችግሮችን በውይይትና በምክክር በመፍታት ጠንካራ ሥርዓት ለመገንባት በጋራ መስራት ይገባል - አቶ ከፍያለው ተፈራ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 5/2018(ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል አሁን ያሉ ችግሮችን በውይይትና በምክክር በመፍታት ጠንካራ ሥርዓት ለመገንባት በጋራ መስራት እንደሚገባ የብልጽግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከፍያለው ተፈራ ገለጹ።

በክልሉ ዘላቂ ሰላም ማስፈን በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ተካሂዷል። 


 

በመድረኩ ላይ ምሁራን፣ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችና ወጣቶች ተገኝተዋል።

የብልጽግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከፍያለው ተፈራ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በክልሉ ዘርፈ ብዙ ስኬቶች የተመዘገበበት የልማት ስራ ተከናውኗል።

በተለይም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ሥራዎች የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መልኩ መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።

ይሁን እንጂ ከሰላም አንጻር በክልሉ የተስተዋለው ችግር የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ልማት ሥራዎችን በሚፈለገው ፍጥነት ለማስኬድ እንቅፋት መፍጠሩን አንስተዋል። 

"ችግሮችን በውይይትና በምክክር በመፍታት ጠንካራ ሥርዓት ለመዘርጋትና ልማትን ለማፋጠን በጋራ መቆም ይገባል" ብለዋል። ለዚህም ኃላፊነቱ የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ባለድርሻ አካላት መሆኑን አስገንዝበዋል።

በልማትና ሰላም ላይ አተኩሮ ከሚሰራ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት የመጡት ገረሱ ቱፋ (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ የመነሻ ጽሑፍ አቅርበዋል። 

እሳቸውም ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን እያንዳንዱ ዜጋ የራሱ የሆነ ድርሻ እንዳለውና ሰላም ለልማት መሰረት መሆኑን አስረድተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በክልሉ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ልማት ለማከናወን ሰላም ቀዳሚ ተግባር መሆን እንዳለበት አንስተዋል።

ማንኛውም ችግር ዘመኑን በሚመጥን መልኩ በሰለጠነ ውይይትና በንግግር ብቻ መፈታት ይኖርበታል ያሉት ተሳታፊዎቹ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችና ወጣቶች ለሰላም ግንባታው ግንባር ቀደም ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ አመልክተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም