ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ የሴቶች ውሳኔ ሰጪነት ድርሻ ከፍተኛ ዕድገት እያስመዘገበ ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 5/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ የሴቶች ውሳኔ ሰጪነት ድርሻ ከፍተኛ ዕድገት እያስመዘገበ መሆኑን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሰለሞን አየለ ገለፁ።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ከሴቶች ክንፍና ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ''ፍትሀዊ ውክልና ለዲሞክራሲያዊ ምርጫ'' በሚል መሪ ሃሳብ የሴቶች ቀንን አክብሯል።


 

በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሰለሞን አየለ፤ በኢትዮጵያ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች የሴቶች ውሳኔ ሰጪነት ሚና በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎችም በሚቀርጿቸው ፖሊሲዎችና ፕሮግራሞች የሴቶችን ውሳኔ ሰጭነትና ተሳትፎ ማሻሻል እንደሚኖርባቸው ገልጸዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትም የሴቶችን ተሳትፎና ውሳኔ ሰጪነት ድርሻ ለማጠናከር አበክሮ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።


 

የጋራ ምክር ቤቱ የሴቶች ክንፍ ሰብሳቢ እፀገነት ተስፋዬ በበኩላቸው፤ ባለድርሻ አካላት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትና የውሳኔ ሰጪነት ድርሻ ለማጎልበት በትኩረት መስራት ይገባቸዋል ብለዋል።

የፖለቲካ ፓርቲ አደረጃጀቶችም የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ውሳኔ ሰጪነት ማረጋገጥ የሚያስችል ምቹ ምኅዳር መፍጠር እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።


 

የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ነቢሃ መሀመድ፤ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ የሴቶች ተሳትፎና ውሳኔ ሰጪነት ድርሻ ዕድገት እያስመዘገበ ነው ብለዋል።

በቀጣይም የሴቶችን የፖለቲካ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ውሳኔ ሰጪነት ድርሻ ለማሻሻል የመጡ ለውጦችን የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባ አንስተዋል።


 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሥራ አመራር ቦርድ አባል ነሲም አሊ፤ የምርጫ ሂደት ፍትሕዊነትን ለማረጋገጥ የህብረተሰቡ ግማሽ አካል የሆኑት ሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ ያስፈልጋል ብለዋል።

ቦርዱም የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ የሚያስችል የማበረታቻ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም