የጤና አገልግሎት ጥራትና ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የጤና ባለሙያዎች የማይተካ ሚናቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የጤና አገልግሎት ጥራትና ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የጤና ባለሙያዎች የማይተካ ሚናቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 5/2018(ኢዜአ)፦ የጤና አገልግሎት ጥራትንና ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የጤና ባለሙያዎች የማይተካ ሚናቸውን እንዲያጠናክሩ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ አስገነዘቡ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ለ54ኛ ዙር ያስተማራቸውን 263 የህክምና ተማሪዎችን አስመርቋል።
ኮሌጁ በአሁኑ ወቅት በሕክምና፣ በፋርማሲ፣ በሕብረተሰብ ጤና እና በሌሎችም ዘርፎች ከ5 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በመደበኛነት እያስተማረ ይገኛል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚሁ ወቅት፣ የጤና አገልግሎት ጥራትን ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የጤና ባለሙያዎች የማይተካ ሚናቸውን ማጠናከር እንዳለባችው ገልጸዋል።
በጤናው ዘርፍ የፖሊሲ፣ የሪፎርም እና የአዋጅ ማሻሻያዎች እየተከናወኑ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ የጤና ባለሙያዎች በእነዚህ የለውጥ ስራዎች ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ሚናቸውን እንዲያጠናክሩ አሳስበዋል።
ተመራቂዎችም በተሰማሩበት የሥራ መስክ ሁሉ ሙያዊ ሥነ-ምግባርን በመጠበቅ እና በርህራሄ ማገልገል እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።
በጤናው ዘርፍ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን ወደ እድል በመቀየር አዲስ አስተሳሰብ፣ አሰራርና አገልግሎትን የሚያስፋፉ የፈጠራ ስራዎችን በማጎልበት ሚናቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ባለፉት 75 አመታት በአገሪቱ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች ከፍተኛ ተጽእኖ የፈጠሩ 300 ሺህ የሚደርሱ ምሩቃንን አፍርቷል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ከጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ጋር በመቀናጀት ብቁ የጤና ባለሙያዎችን በማፍራትና የሕክምና አገልግሎት በመስጠት ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት በአገር አቀፍ ደረጃ በማስፋፋት ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸዋል።
ከከተሜነትና የአናናር ዘይቤ ለውጥ ጋር ተያያዞ አስፈላጊ የሆኑ የህክምና አገልግሎቶችን ለማስፋፋት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችንም አንስተዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ራሄል አርጋዉ(ዶ/ር) የህክምና ትምህርቱን ከወቅቱ ቴክኖሎጂ ጋር የዘመነ ለማድረግ በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ኮሌጁ በአሁኑ ወቅት በቅድመና ድህረ ምረቃ በ116 መርሃ-ግብሮች ትምህርት እየሰጠ ሲሆን፣ ከጠቅላላ ተማሪዎቹ መካከልም 47 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውን አስታውቀዋል።
የዘንድሮ ተመራቂዎች 98 በመቶ የመውጫ ፈተና ማለፋቸው የጤና ሳይንስ የትምህርት ጥራት ለማስጠበቅ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ማሳያ ነው ብለዋል።
ከተመራቂዎች መካከል አስተያየታቸውን ለኢዜአ የገለጹት የህክምና ባለሙያዎች በተማሩት ሙያና በገቡት ቃልኪዳን መሰረት ማህበረሰቡን ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ የሆነችው ዶክተር ሜሮን ለገሰ እና ሌላው ተመራቂ ዶክተር አገኘሁ በየነ ወቅቱ ከሚጠይቀው የእውቀትና የክህሎት ደረጃ ጋር ራሳቸውን በማብቃት በሙያቸው ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።