ቀጥታ፡

ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የሰላም ዘብና አምባሳደሮች እንሆናለን - በዲዲአር ፕሮግራም ውስጥ ያለፉ አካላት

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 5/2018(ኢዜአ)፦ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የሰላም ዘብና አምባሳደሮች እንደሚሆኑ በዲዲአር ፕሮግራም ውስጥ ያለፉ በተለምዶ አርሚ 70 ተብለው የሚጠሩ አባላት ገለፁ።

በአዋሽ አርባ ጊዜያዊ የዲሞቢላይዜሽን ማዕከል፤ በሱዳን የቆዩ እና የሰላም አማራጭን ተቀብለው ወደ አገራቸው የተመለሱ፣ ከቀድሞ ህወሃት ጎን የነበሩና በተለምዶ አርሚ 70 እየተባሉ የሚጠሩ አባላት የተሃድሶ ሥልጠና ማጠቃለያ መርኃ ግብር ተካሂዷል።


 

በብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን አማካኝነት በዲዲአር ፕሮግራም ውስጥ ያለፉ በተለምዶ የአርሚ 70 ተብለው የሚጠሩ የቀድሞ ተዋጊዎች የሰላም ዘብና አምባሳደሮች ለመሆን ቃል በመግባት ባለ ዘጠኝ ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተዋል።

በዚህም ቀደም ሲል በኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች ሀገራቸውን ሲያገለግሉ የቆዩና በሱዳን የሰላም ማስከበር ግዳጅ ላይ የነበሩ መሆናቸውም ተገልጿል።

ሆኖም በወቅቱ በነበረው የፖለቲካ ውጥረትና በተሰራጩ ስጋቶች ምክንያት በሱዳን ጥገኝነት ጠይቀው በተለምዶ አርሚ 70 ተብሎ የሚጠራውን ተቀላቅለው እንደነበር በመግለጫቸው አስታውሰዋል።

ግጭት የሰውን ሕይወት የሚቀጥፍ፣ ኢኮኖሚን የሚያናጋና ማህበራዊ ጠባሳ የሚተው ነው ሲሉም በአቋም መግለጫቸው አስታውቀዋል ።

ስለሆነም ግጭቶችን በውይይት የመፍታት ባህል እንዲዳብርና የሚቀጥለው ትውልድ ግጭትን የሚጸየፍ እንዲሆን የሰላም ሰባኪ ለመሆን ቃል ገብተዋል።

የትግራይ ህዝብ ከግጭት አዙሪት ወጥቶ አስተማማኝ ሰላም እንዲያገኝ እንደ ሰላም አምባሳደር በትጋት እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።

የተሃድሶ ሂደቱ በመጀመሩ መንግሥትንና የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽንን አመስግነው፤ ዕድሉ ለሌሎችም ተደራሽ እንዲሆንም ጠይቀዋል።

ማንኛውም የሃሳብ ልዩነት በሰላማዊ መንገድና በውይይት ብቻ እንዲፈታ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ በድጋሚ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም