የፖለቲካ ፓርቲዎች አማራጭ የፖሊሲ ሃሳብና ፕሮግራማቸውን ለህዝብ የሚያስተዋውቁበት ሰፊ መድረክ እየፈጠርን ነው - ኢዜአ አማርኛ
የፖለቲካ ፓርቲዎች አማራጭ የፖሊሲ ሃሳብና ፕሮግራማቸውን ለህዝብ የሚያስተዋውቁበት ሰፊ መድረክ እየፈጠርን ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 5/2018(ኢዜአ)፦ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አማራጭ የፖሊሲ ሃሳብና ፕሮግራማቸውን ለህዝብ የሚያስተዋውቁበት ሰፊ መድረክ እየፈጠሩ እንደሚገኙ ኢዜአ ያነጋገራቸው የመገናኛ ብዙኅን ኃላፊዎች ገለጹ።
መገናኛ ብዙሃን የዜጎችን የፖለቲካ ንቃተ-ህሊና በማሳደግና የፖለቲካ እሳቤዎቻቸውን በነፃነት እንዲያንሸራሸሩ ምቹ መድረክ በመፍጠር ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በዋና ምሰሶነት ያገለግላሉ።
በተለይም በምርጫ ወቅት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እኩል የክርክርና የዘገባ ሽፋን እንዲያገኙ በማድረግ ህዝቡ በቂ መረጃ ኖሮት በትክክለኛ ውሳኔ ድምፅ የሚሰጥበትን የማስተማር ኃላፊነት ይወጣሉ።
የመገናኛ ብዙሃን ኃላፊዎችና ጋዜጠኞች ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ለአንድ ሀገር የምርጫ ሥርዓት ነፃ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊነት መገናኛ ብዙኃን ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የዜና ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ተፈራ በቀለ እንደገለጹት፤ መገናኛ ብዙኅን ለምርጫ ሂደት ስኬት ገንቢ ሚና የሚወጣ የዴሞክራሲ ሥርዓት መገንቢያ መሳሪያ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትም ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማነት የምርጫ ዴስክ በማቋቋም የቅድመ ምርጫ፣ የምርጫ ወቅትና የድህረ ምርጫ ዕቅድ በማውጣት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
በዚህም የምርጫ ዘገባዎችን በዜና እና ዜና ነክ ጉዳዮች ላይ መረጃዎችን በጥራትና በፍጥነት በማጠናቀር በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ተደራሽ እያደረገ መሆኑን አንስተዋል።
በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የምርጫ ዴስክ ሰብሳቢ በክሪ ናስር፤ ከስድስተኛው የምርጫ ተሞክሮ በመነሳት ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬት የክርክር መድረክና የዘገባ ሥራዎችን በማዘጋጀት ተደራሽ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
በየፖለቲካ ፖርቲዎች መካከል በሃሳብ የበላይነት የተመሰረተ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓትን ለማጎልበት በተለያዩ ቋንቋዎች የንግግር ባህል ማጎልበት የሚያስችል መድረክ እየፈጠሩ እንደሚገኙ አንስተዋል።
የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ ዳዊት መስፍን በበኩላቸው፤ መገናኛ ብዙኅን ለተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚፈጥሯቸው መድረኮች ዜጎች አማራጭ የፖሊሲ ሃሳቦችን እንዲገነዘቡ በማድረግ በኩል ወሳኝ ሚና አላቸው ብለዋል።
በዚህም ፍትሐዊ የአየር ሰዓት ድልድል በመፍጠር ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖሊሲ አማራጫቸውን በነፃነት ለህዝብ የሚሸጡበት መድረክ ተመቻችቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ የሚሰጠው መራጩ ዜጋ ይሆነኛል የሚለውን የፖለቲካ ፓርቲ ድምፅ መስጠት የሚችልበትን ወሳኝ ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫም የኢትዮጵያን በሃሳብ የበላይነት የተመሰረተ የፖለቲካ ባህል መገንባት የሚያስችል ምቹ የመገናኛ ብዙኅን ምኅዳር በመፍጠር እየተሰራበት መሆኑን አስረድተዋል።
መገናኛ ብዙኅን የፈጠሯቸው የፖሊሲ አማራጭ የክርክር መድረኮች ከዚህ ቀደም የነበረውን የመወቃቀስና መካሰስ አካሄድ በመቀየር ተስፋ ሰጪ የዴሞክራሲ ምኅዳር እየተፈጠረ መሆኑን አንስተዋል።
በቀጣይም ለተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፍትሐዊ የአየር ሰዓትና የዘገባ ሽፋን በመስጠት በሃሳብ የበላይነት ለተመሰረተ የፖለቲካ ፉክክር መጎልበት የሚጠበቅባቸውን ገንቢ ሚና መወጣታቸውን እንደሚያጠናክሩ አረጋግጠዋል።