ቀጥታ፡

ተመራቂዎች በመልካም ስነምግባርና በሃላፊነት ስሜት ህዝባቸውን ማገለግል ይጠበቅባቸዋል - ዶክተር ደረጀ ዱጉማ

ነቀምቴ፤ መጋቢት 5/2018(ኢዜአ)፦ ተመራቂዎች በላቀ ሥነ-ምግባርና በኃላፊነት ስሜት ሕዝባቸውን ሊያገለግሉ እንደሚገባ የጤና ሚኒስትር ደኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ ገለጹ።

ወለጋ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ያሰለጠናቸውን 792 ተማሪዎችን ዛሬ በደመቀ ሁኔታ አስመርቋል።

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ በበየነ-መረብ መልእክታቸውን ያስተላለፉት የጤና ሚኒስትር ደኤታው ዶክተር ደረጄ፣ ተመራቂዎች የቀሰሙትን ዕውቀት ከዘመኑ ጋር በማዛመድ ለሀገሪቱ የእድገት ጉዞ የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።


 

በተለይ የጤና ዘርፍ ተመራቂዎች፤ ሙያው ከፍተኛ ሰብአዊነትን የሚጠይቅ መሆኑን ጠቅሰው፣ የእናቶችንና የሕጻናትን ሕይወት የመታደግ ከባድ አደራ በላቀ ሥነ-ምግባርና በኃላፊነት ስሜት እንዲወጡ አስገንዝበዋል።

የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ተስፋዬ ለማ(ዶ/ር) እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው በነቀምቴ፣ በሻምቡ እና በጊምቢ ካምፓሶቹ ብቁና የተማረ የሰው ኃይል በማፍራት በኩል ያለበትን ሀገራዊ ኃላፊነት እየተወጣ ነው።

ተማሪዎቹ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ባገኙት ትምህርትና ልምድ ሕብረተሰባቸውን ለማገልገል ቆርጠው መነሳት ይገባቸዋል ብለዋል።

የነቀምቴ ከተማ ከንቲባ መሰረት ኃይሉ በበኩላቸው፤ ውጤቱ የቤተሰብና የመላው ማኅበረሰብ ድካም መሆኑን ገልጸዋል።

በዕለቱ በሕክምና ትምህርት ክፍል 3 ነጥብ 5 ውጤት ያስመዘገበችው ዶክተር ሎዛ መድኃኒቴ እንደተናገረችው፣ በዩኒቨርሲቲው በቀሰመችው እውቀት ሴቶችና ሕጻናትን በተሻለ ሁኔታ ለማገልገል ዝግጁ መሆኗን ገልጻለች።

ሌላው 3 ነጥብ 87 ውጤት በማምጣት የዋንጫና የሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኖ የተመረቀው ተማሪ ሳሙኤል ኃይሌ፤ ጊዜውን በአግባቡ በመጠቀሙ ለውጤት መብቃቱን በዩኒቨርሲቲ ቆይታው ባገኘው ልምድና ትምህርት ማኅበረሰቡን በትጋት ለማገልገል መዘጋጀቱን ተናግሯል።

ዩኒቨርሲቲው ዛሬ ካስመረቃቸው መካከል በመጀመሪያ ዲግሪ 661፣ በሁለተኛ ዲግሪ 125 እና የዶክትሬት ዲግሪ PhD) 6 ተማሪዎች መሆናቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም