ቀጥታ፡

ትግራይ ክልል ለልማትና ሰላም ግንባታ የተሰለፉ ወጣቶችን ትፈልጋለች - አብረሃም በላይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 5/2018(ኢዜአ)፦ ትግራይ ክልል ለልማትና ሰላም ግንባታ የተሰለፉ ወጣቶችን ትፈልጋለች ሲሉ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብረሃም በላይ (ዶ/ር) ገለጹ።

በአዋሽ አርባ ጊዜያዊ የዲሞቢላይዜሽን ማዕከል፤ በሱዳን የቆዩ እና የሰላም አማራጭን ተቀብለው ወደ አገራቸው የተመለሱ፣ ከቀድሞ ህወሃት ጎን የነበሩና በተለምዶ አርሚ 70 እየተባሉ የሚጠሩ አባላት የተሃድሶ ሥልጠና ማጠቃለያ መርኃ ግብር ተካሂዷል።

በመድረኩ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብረሃም በላይ (ዶ/ር) እና የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዲየር ጄኔራል ደርቤ መኩሪያ ተገኝተዋል።

የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብረሃም በላይ (ዶ/ር) የሰላም አማራጭን በመከተል ወደ ሀገራቸው በመመለስ የተሀድሶ ስልጠና በመከታተላቸው አድንቀዋል።

የፌዴራል መንግስት በትግራይ ሰላምን ለማፅናት እና ልማትን ለማረጋገጥ ያልሞከረው ሙከራ እንደሌለ ጠቁመው፤ ቆሞ ቀሩ የቀድሞ ህወሓት ቡድን ከህዝብ በላይ ነኝ በሚል እሳቤ አሁንም እንቅፋት እየሆነ መምጣቱን አብራርተዋል።

ቡድኑ በሚያሰራጨው የሃሰት ወሬ ህዝቡ ሊደናገር አይገባም ያሉት ዶክተር አብርሃም፤ ከመንግስት ጎን ሆኖ ልማቱን እንዲያፋጥን ጥሪ አቅርበዋል።

ይህ ቆሞ ቀር ቡድን ሥልጣን ላይ በቆየበት ወቅት ሀገር ከማልማት ይልቅ የግል ጥቅምን ያስቀደመ እንደነበር አስታውሰዋል።

የፌዴራል መንግስት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት የሚጠበቅበትን ተግባራት ሁሉ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

ወጣቱ ከግጭት አውድማ ወጥቶ ሰላምን መምረጡ ለራሱም፣ ለክልሉም ሆነ ለሀገሩ ትልቅ ስኬት መሆኑ ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅት ትግራይ ክልል የሚያስፈልጋት ለልማትና ለሰላም ግንባታ የተሰለፈ ወጣት እንጂ ለግጭት የሚማገድ እንዳልሆነም አስገንዝበዋል።

በሀገሪቷ በማንኛውም አካባቢ የመስራትና የመንቀሳቀስ መብቱ የተጠበቀ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀድሞ የህወሓት ቡድን የሚነዙ የተሳሳቱ አሉባልታዎችን ውድቅ አድርገዋል።

ትግራይን ወደ ፊት ማራመድ የሚቻለው በግጭት ሳይሆን ሰላምን መሠረት ባደረገ ኃይል ብቻ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዲየር ጄኔራል ደርቤ መኩሪያ በበኩላቸው፤ እነዚህ ወገኖች ቀደም ሲል በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ ያገለገሉ፣ በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች የተሳተፉና በሱዳን ድንበር አካባቢ የነበሩ ናቸው ብለዋል።

የሰላምን አማራጭ በመቀበል ወደ ማዕከሉ የመጡትን ዜጎች የመለየት፣ የማረጋገጥና የመመዝገብ ሥራ በጥንቃቄ ተከናውኖ ወደ ተሃድሶ ሥልጠና እንዲገቡ መደረጉን ነው ያስረዱት።

የተሃድሶ ሥልጠና ዓላማ ከግጭት አስተሳሰብ ተላቅቀው የሰላምና የልማት ኃይል እንዲሆኑ ማድረግ አንዱ መሆኑን አመልክተው፤ እንዲሁም በማህበረሰቡ ውስጥ ሲቀላቀሉ ሰላምን የሚያፀኑ እንዲሆኑ ለማድረግ ነው ብለዋል።

በቀጣይም ሰፋፊና ጥልቀት ያላቸው የተሃድሶ ሥልጠናዎች እንደሚሰጡ ጠቁመዋል።

የሰላም አምባሳደር በመሆን የሀገርን አንድነትና ልማት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም