ምሩቃን በትምህርት ቆይታቸው በቀሰሙት እውቀትና ክህሎት ሀገርና ህዝብን በቅንነት ማገልገል አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
ምሩቃን በትምህርት ቆይታቸው በቀሰሙት እውቀትና ክህሎት ሀገርና ህዝብን በቅንነት ማገልገል አለባቸው
ሚዛን አማን፤ መጋቢት 5/2018(ኢዜአ)፦ ምሩቃን በትምህርት ቆይታቸው በቀሰሙት እውቀትና ክህሎት ሀገርና ህዝብን በቅንነት በማገልገል የተጀመረውን ሀገራዊ የእድገት ጉዞ ሊያፋጥኑ እንደሚገባ ተመለከተ።
ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 404 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ የተገኙት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የመንግሥት ዋና ተጠሪ ፍቅሬ አማን መመረቅ አዲስ የሕይወት ምዕራፍ መከፈትና ለሀገር ግንባታ የዜግነት ኃላፊነት መወጣት ጅማሮ ነው ብለዋል።
ተመራቂዎች በቀጣይ ወደ ስራው ዓለም ሲገቡ ሀገርና ህዝብን በታማኝነትና በቅንነት በማገልገል ሙያዊ ግዴታቸውን በታማኝነት ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ለዚህም በትምህርት ቆይታቸው በቀሰሙት እውቀትና ክህሎት መሠረት ሥነ ምግባር የተላበሰ አገልግሎት በመስጠት ሀገራዊ የለውጥና የዕድገት ጉዞን ማጠናከር እንዳለባቸው ገልጸዋል።
በተለይ የጤና ተመራቂዎች ሀገራችን በምትከተለው በሽታን ቀድሞ የመከላከልና አክሞ የማዳን ሥርዓት ላይ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ በአጽንኦት ተናግረዋል።
የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዋቆ ገዳ(ዶ/ር) በበኩላቸው ተመራቂዎች የነገ የማኅበረሰቡ ተስፋ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ያካበቱትን ዕውቀትና ክህሎት በቀጣይ ወደ ተግባር በመቀየር ሀገራዊ የለውጥና የዕድገት ጉዞ ላይ ሚናቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
ዩኒቨርሲቲው ለመጀመሪያ ጊዜ ያስመረቃቸው 21 የሜዲካል ዶክተሬት ዲግሪ ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ የመውጫ ፈተና በማምጣት የተመረቁ መሆናቸውንም አመልክተዋል።
ከተመራቂዎቹ መካከል ዶክተር እፀገነት አያለው 3 ነጥብ 68 በማምጣት በማዕረግ የተመረቀች ሲሆን ትኩረት ሰጥቶ በመማር ከድካም በኋላ የተሻለ ውጤት ማስመዝገቧን ተናግራለች።
ስትመረቅ ቃል በገባችው መሠረት ያስተማራትን ማኅበረሰብ በቅንነት ለማገልገል መዘጋጀቷን ገልጻለች።
ከፋርማሲ ትምህርት ክፍል በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቀው መሐመድ ሐሰን በበኩሉ ሙያዊ ኃላፊነቴን በብቃት ለመወጣት ተዘጋጅቻለሁ ብሏል።
መማራችን ትርጉም እንዲኖረው ጤናማ ማኅበረሰብ በመፍጠር ለሀገር ልማት ጉልህ አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅብናል ነው ያለው።