በአዳማ ከተማ በሦስት ክፍለ ከተሞች መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በይፋ ስራ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በአዳማ ከተማ በሦስት ክፍለ ከተሞች መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በይፋ ስራ ጀመረ
አዳማ፤ መጋቢት 5/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ ሦስት ክፍለ ከተሞች መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በይፋ ስራ ጀመረ።
የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመንና ብልሹ አሰራርን ለመቅረፍ ታስቦ የተጀመረው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ በአዳማ ከተማ በሚገኙ አባገዳ፣ ቦሌ እና ዳቤ ክፍለ ከተሞች በይፋ ስራ ጀምረዋል።
በማስጀመሪያ ስነ-ሥርዓቱ የተገኙት የፌዴራል ፐብሊክ ሰርቪስ ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ(ዶ/ር) እንዳሉት የማዕከሉ ወደ ስራ መግባት በመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የነበረውን ችግር እየቀረፈ ነው።
በአዳማ የተጀመረው ተሞክሮ በፌዴራልና በክልሎችም ለማስፋፋት እንደ ምሳሌ የሚወሰድ በመሆኑ ኮሚሽኑ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
የመሶብ አገልግሎት መልካም አስተዳደርን ከማስፈን ባለፈ ዜጎች ከመንግሥት የሚፈልጉትን አገልግሎት የሚያገኙበት ማዕከል መሆኑን ጠቅሰው በአዳማ የተጀመረው ማዕከላቱን የማስፋፋት ስራ የሚበረታታ መሆኑን አንስተዋል።
የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አወሉ አብዲ፣ በክልሉ በመጀመሪያው ዙር አገልግሎቱ በተጀመረባቸው ከተሞች ከ500 ሺህ በላይ ዜጎች ተጠቃሚ ሆነዋል ብለዋል።
አሁን እየተካሄደ በሚገኘው በሁለተኛው ዙር ማዕከላቱን አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ደግሞ አዳማን ጨምሮ በ26 የክልሉ ከተሞች አገልግሎቱ ስራ ጀምሯል ነው ያሉት።
አገልግሎቱ በቴክኖሎጂ የታገዘ በመሆኑ፣ የመልካም አስተዳደር ችግርንና እንግልትን ለመቀነስ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ተናግረዋል።
በሦስተኛ ዙር መርሃ ግብር ደግሞ አገልግሎቱን ወደ 60 ከተሞች ለማስፋፋት የታቀደ ሲሆን፣ ህብረተሰቡ ባለበት ቦታ ሆኖ አገልግሎት የሚያገኝበትን ስርዓት ለመዘርጋት ግብ ተቀምጦ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
አዳማ ከተማ አገልግሎቱን ቀድማ በማስፋፋት ለክልሉ ምሳሌ ሆናለች ያሉት አቶ አወሉ የህዝቡን የአገልግሎት እርካታ ለማረጋገጥ ርብርብ እየተደረገ መሆኑ ገልጸዋል።
በቀጣይም ዜጎች ካሉበት ሆነው በቀጥታ አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ የሚሰራ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።
የአዳማ ከተማ ከንቲባ ኃይሉ ጀልዴ በበኩላቸው በከተማ ደረጃ ከ130 በላይ አገልግሎቶች በአንድ ማዕከል እየተሰጡ መሆኑን ገልጸዋል።
ዛሬ በተመረቁት ሦስት ክፍለ ከተሞች ደግሞ 110 የሚሆኑ አገልግሎቶች ለህዝቡ ክፍት መሆናቸውን ጠቅሰው ይህም የዜጎችን እርካታ ከመጨመር ባለፈ የኢንቨስትመንት ፍሰቱ እንዲጨምር ያስችላል ብለዋል።