ቀጥታ፡

በሸገር ከተማ ባለፉት ስምንት ወራት 25 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ገቢ ተሰበሰበ

ሸገር፤ መጋቢት 5/2018(ኢዜአ)፦ በሸገር ከተማ ግብርን በቴክኖሎጂ ታግዞ በመሰብሰብና የተሻሻሉ የታክስ ህጎችን በመተግበር ባለፉት ስምንት ወራት 25 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን የከተማው ገቢዎች ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የሸገር ከተማ ገቢዎች ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ መልካሙ አምባው ለኢዜአ እንደተናገሩት በከተማው የሚሰበሰብ ገቢን ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላት ጋር የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።

ሸገር ከተማ ከመቋቋሙ በፊት ሲሰበሰብ የነበረው ገቢ ከ5 ቢለየን ብር በታች እንደነበርና የከተማው መቋቋምን ተከትሎ የገቢው መጠን እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።

ባለፈው ዓመት ከከተማው 24 በሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታውሰው በተያዘው ዓመትም 39 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱንና ባለፉት ስምንት ወራት ብቻ 25 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን አስታውቀዋል።

ገቢው ከማዘጋጃ ቤታዊ፣ ቀጥተኛና ቀጥተኛ ካልሆኑ የገቢ አርዕስቶች የተሰበሰበ መሆኑን ጠቁመው፣ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ብልጫ እንዳለውም ተናግረዋል።

የግብር አሰባሰብ ሥራው በቴክኖሎጂ መደገፉ፣ የተሻሻሉ የታክስ ህጎች ተግባራዊ መደረጋቸውና የአገልግሎት አሰጣጡ መዘመኑ ዘንድሮ ከፍተኛ ገቢ እንዲሰበሰብ አስችሏል ብለዋል።

የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ላይ የተሰጠው ትኩረት፣ የግብር ከፋዮች ቁጥር መጨመርና የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር ማደግ ለገቢው መጨመር ከፍተኛ እገዛ አድርጓል ነው ያሉት።

በዘርፉ ህገ-ውጥ ተግባራትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተደረገ እንቅስቃሴ ለሸጡት እቃ ደረሰኝ ሳይቆርጡ የተገኙ 59 ግብር ከፋይ ነጋዴዎች በገንዘብ መቀጣታቸውን አንስተዋል።

ህግ ተላልፈው በተገኙ 33 የተቋሙ ሠራተኞች ላይም አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን ጠቁመው ተግባሩ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም