ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል ማጃንግ ዞን በመኸሩ ከ52ሺህ 900 ቶን በላይ የቡና ምርት ተገኝቷል

ጋምቤላ፤ መጋቢት 5/2018(ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ክልል ማጃንግ ዞን በመኸሩ ከ52ሺህ 900 ቶን በላይ የቡና ምርት መገኘቱን የዞኑ የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት መምሪያ አስታወቀ።

በዞኑ ከተመረተው ቡና ከ42ሺህ 624 ቶን በላይ የታጠበና ቅሽር የቡና ምርት ለማዕከላዊ ገቢያ ለማቅርብ እየተሰራ እንደሚገኝም መምሪያው ገልጿል።


 

በመምሪያው የቡና፣ ሻይና ቅመማቅመም ልማትና ግብይት ቡድን መሪ ሲሳይ በላይነህ፤ በክልሉ ማጃንግ ዞን በዘንድሮው መኸር 52ሺህ 962 ቶን የቡና ምርት መገኘቱን ገልጸዋል።።

በዞኑ በሚገኙ የጎደሬና መንገሺ ወረዳዎች በአርሶ አደሩና በባለሃብቶች ከለማው 68ሺህ 637 ሄክታር የቡና ተክል የተገኘ ምርት መሆኑንም ተናግረዋል።


 

በዞኑ በዘንድሮው የምርት ዘመን የተገኘው የቡና ምርት ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ17ሺህ 186 ቶን ብልጫ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

ለተገኘው ውጤትም በዞኑ የተስተካከል የዝናብ ስርጭትና የአየር ፀባይ በመኖሩና የተጠናከረ የቡና ተክልና እንክብካቤ ስራዎች መከናወናቸው እንዲሁም አርሶ አደሩ ከቡና ልማት የሚያገኘው ጥቅም እያደገ በመምጣቱ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም