ቀጥታ፡

የኃይማኖት ተቋማት የሰላምና አብሮነት እሴቶችን በማፅናትና በትውልድ ግንባታ ላይ የላቀ ሚናቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል

ሐረር፤ መጋቢት 5/2018(ኢዜአ)፦ የኃይማኖት ተቋማት የሰላምና አብሮነት እሴቶችን በማፅናትና ጥሩ ስብእና የተላበሰ ትውልድ መገንባት ላይ የላቀ ሚናቸውን ማጠናከር እንደሚገባቸው የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ።

የኢትዮጵያ የወንጌል አማኞች ህብረት ለሐረር ካውንስል ቅርንጫፍ የሃይማኖት አባቶች የተዘጋጀ የምክክር መድረክ በሀረር ከተማ ተካሂዷል።

በመድረኩ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ፤ የሃይማኖት አባቶች ምዕመናንን በማስተማር መልካም ስነ ምግባር ያላቸውን ዜጎች ለማፍራት በሚደረገው ጥረት የላቀ አበርክቶ እንዳለቸው አንስተዋል።


 

በአስተምህሮቶቻቸው የወንድማማችነትና እህትማማችነት እሴቶችን በማጎልበት በኩል እየሰሩ መሆኑን ጠቁመው የሰላምና አብሮነት እሴቶችን በማፅናትና ጥሩ ስብእና የተላበሰ ትውልድ መገንባት ላይ የላቀ ሚናቸውን ማጠናከር ይገባቸዋል ብለዋል።

የመድረኩ አላማም የህዝብ ተጠቃሚነትን የሚያጎለብቱ፣ ሀገርን የሚገነቡና የሚያለሙ ሃሳቦች እንዲንጸባረቁበት በማሰብ መሆኑን ጠቁመው ለሰላም፣ ለሀገርና የትውልድ ግንባታ በአብሮነት መስራታችን ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ነው ያሉት።

የመድረኩ ተሳታፊዎችም በክልሉ የተከናወኑ የልማት ስራዎች አበረታች መሆናቸውን አንስተው የሃይማኖት ተቋማት ሰላምና አንድነትን በማስተማር ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ልማት ለማምጣት አስተዋጿቸውን እንደሚያጎለብቱ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም