ቀጥታ፡

የፖሊስ ሰራዊት ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ያስጠሩ ስፖርተኞችን በማፍራት የማይተካ ሚና እየተወጣ ይገኛል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 5/2018 (ኢዜአ)፦ የፖሊስ ሰራዊት የሀገርን ስም የሚያስጠሩና ሰንደቅ ዓላማን በዓለም አቀፍ መድረኮች ከፍ የሚያደርጉ ዝነኛ ስፖርተኞችን በማፍራት የማይተካ ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

2ኛው ከተማ አቀፍ የአዲስ አበባ ፖሊስ ስፖርት ውድድርና ፌስቲቫል "ተልዕኮን በጀግንነት፣ ስፖርትን በውጤት" በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ በአበበ በቂላ ስታዲየም ተጀምሯል።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት የስፖርት ውድድር እና ፌስቲቫሉ በስድስት የስፖርት አይነቶች እንደሚካሄድ ገልጸዋል።


 

ውድድር እና ፌስቲቫሉ ከዛሬ ጀምሮ ለሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት በከተማዋ በሚገኙ የተለያዩ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

የፖሊስ ሰራዊት ከሰላም ጥበቃ ተልዕኮው ጎን ለጎን፣ የሀገርን ስም የሚያስጠሩና ሰንደቅ ዓላማን በዓለም አቀፍ መድረኮች ከፍ የሚያደርጉ ዝነኛ ስፖርተኞችን በማፍራት ረገድ የማይተካ ሚና እያበረከተ ይገኛል ብለዋል።

ከንቲባዋ በመልዕክታቸው ይህ የሰራዊቱ ተሳትፎ በቀጣይም ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም