በጋምቤላ ክልል በመጪው የመኸር ወቅት ከ180 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ ለማልማት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል በመጪው የመኸር ወቅት ከ180 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ ለማልማት እየተሰራ ነው
ጋምቤላ፤ መጋቢት 5/2018 (ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ክልል በመጪው የመኸር እርሻ ከ180 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ ማሳ በተለያዩ ሰብሎች ለማልማት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ ስነ- ምህዳርን መሰረት ያደረገ ስራ ለማከናወነ የምርጥ ዘርና የማዳበሪያ ግብዓት ለማቅረብም እየተሰራ መሆኑን ቢሮው ገልጿል።
የቢሮው ኃላፊ አቶ አንድሪው ቱት ለኢዜአ እንደገለጹት፤ እንደ ሀገር የግብርና ትራንስፎርሜሽን እቅዱን ውጤታማ በማድረግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ለተያዘው ግብ ስኬት እየተሰራ ነው።
በ2018/19 የመኸር እርሻ ከ180 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በማልማት ከ 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሳብ ታቅዶ ወደ ትግበራ ምዕራፍ መገባቱን ተናግረዋል።
በመኸር ወቅት ለማልማት የታቀደው መሬት ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ፤ በ8 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ ሲሆን በምርት መጠን ደግሞ የ600 ሺህ ኩንታል ልዩነት ያለው መሆኑን አስረድተዋል።
በዚሁ ወቅት መካናይዝድ የግብርና ቴክኖሎጂን ፣የምርጥ ዘርና ሌሎች ግብዓቶችን በስፋት በመጠቀም ምርታማነትን ለማሳዳግ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
አሁን ላይ በክልሉ ያለውን ወይና ደጋና ቆላማ ስነ-ምህዳር መሰረት ባደረገ መልኩ የምርጥ ዘር አቅርቦትና ስርጭት ለማከናወን የዘር ግዥ ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
በክልሉ በዘንድሮው የመኸር እርሻ የአፈር ማዳበሪያን በስፋት ጥቅም ላይ በማዋል ምርታማነትን ለማሳደግ ሰፊ የንቅናቄ ስራዎች እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።