ቀጥታ፡

የግብርና ሚኒስቴር ብሔራዊ የሥነ-ምኅዳር ደህንነትን በማስጠበቅ ምርታማነትን የሚያሻሽሉ ብሔራዊ ስትራቴጂዎችን ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 5/2018(ኢዜአ)፦ የግብርና ሚኒስቴር ብሔራዊ የሥነ-ምኅዳር ደህንነትን በማስጠበቅ ምርታማነትን የሚያሻሽሉ ብሔራዊ ስትራቴጂዎችን ይፋ አድርጓል።

ይፋ የተደረጉት ስትራቴጂዎች የብሔራዊ ጥምር ደን እርሻ ልማትና ብሔራዊ የሥነ-ምህዳር ስትራቴጂዎች ናቸው።

በመርሃ ግብሩ የፌዴራልና ክልል ባለድርሻ አካላት፣ የልማት አጋሮች፣ የጥናትና ምርምር ተቋማት የልማት አጋር ድርጅቶች ተወካዮች ተገኝተዋል።

በዚሁ ወቅት የግብርና ሚኒስትር ደኤታ ፕሮፌሰር እያሱ ኤሊያስ፤ የግብርና ዘርፍ በሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የማይተካ ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።


 

ይሁን እንጂ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የአፈር ለምነት መቀነስ፣ የአካባቢ መራቆትና የደን ጭፍጨፋ በግብርና ምርታማነት ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርና የምርታማነት ስልቶች ተፅዕኖን መቋቋም የሚያስችል አስደናቂ ውጤት መመዝገቡን አንስተዋል።

ብሔራዊ የሥነ-ምኅዳር ስትራቴጂውም በአፈር ጤንነት ጥበቃ፣ በውሃ አጠቃቀምና ብዝኅ ህይወት ደኅንነትን በማስጠበቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልጸዋል።

የብሔራዊ የጥምር ደን እርሻ ልማት ስትራቴጂው የደንና የግብርና መልክዓ-ምድራዊ ሥርዓትን በማሻሻል ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ጠቅሰዋል።

ሁለቱም ብሔራዊ ስትራቴጂዎች የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነትና የመሬት ለምነት በማሻሻል የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት አይነተኛ ሚና እንደሚኖራቸው አስረድተዋል።

ለብሔራዊ ስትራቴጂዎቹ ውጤታማነት የልማት አጋሮችና ባለድርሻ አካላት ትብብር ወሳኝ መሆኑም በመድረኩ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም