ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ 263 የህክምና ተማሪዎችን አስመረቀ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 5/2018(ኢዜአ)፡- የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ለ54ኛ ዙር ያስተማራቸውን 263 የህክምና ተማሪዎችን አስመርቋል።

ኮሌጁ በአሁኑ ወቅት በሕክምና፣ በፋርማሲ፣ በሕብረተሰብ ጤና እና በሌሎች ዘርፎች ከ5 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በመደበኛነት እያስተማረ ይገኛል።


 

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ የጤና አገልግሎት ጥራት፣ ተደራሽነትና ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የጤና ባለሙያዎች የማይተካ ሚና አላቸው።

በጤናው ዘርፍ የፖሊሲ፣ የሪፎርም እና የአዋጅ ማሻሻያዎች እየተከናወኑ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ የጤና ባለሙያዎች በእነዚህ የለውጥ ስራዎች ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ሚናቸውን እንዲያጠናክሩ አሳስበዋል።

ተመራቂዎችም በስራቸው ሙያዊ ሥነ-ምግባርን በመጠበቅ እና በርህራሄ ማገልገል እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።


 

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ዩኒቨርሲቲው ከጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ጋር በመቀናጀት ብቁ የጤና ባለሙያዎችን በማፍራትና የሕክምና አገልግሎት በመስጠት ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸዋል።

የዘንድሮ ተመራቂዎች 98 በመቶ የሚሆኑት የመውጫ ፈተና ማለፋቸው የዩኒቨርሲቲውን የትምህርት ጥራትና ስኬት የሚያመላክት መሆኑን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶክተር ራሄል አርጋው የህክምና ትምህርቱን ከወቅቱ ቴክኖሎጂ ጋር ያደገ ለማድረግ በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ኮሌጁ በአሁኑ ወቅት በቅድመና ድህረ ምረቃ በ116 መርሃ-ግብሮች ትምህርት እየሰጠ ሲሆን ከጠቅላላ ተማሪዎቹ መካከልም 47 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም