ቀጥታ፡

ለ"ፊቼ ጫምባላላ" በዓል የሚካሄደው ስፖርታዊ ውድድር በዓሉንና ባህላዊ እሴቶቹን ለማስተዋወቅ እያገዘ ነው

‎ሀዋሳ፤ መጋቢት 5/2018 (ኢዜአ)፡-የሲዳማ ዘመን መለወጫ "ፊቼ ጫምባላላ"ን በማስመልከት በየዓመቱ የሚካሄደው ስፖርታዊ ውድድር በዓሉንና ባህላዊ እሴቶቹን ለማስተዋወቅና ለማጠናከር እያገዘ መሆኑ ተገለጸ።

ለ"ፊቼ ጫምባላላ እሮጣለሁ" በሚል መሪ ቃል ዛሬ በሀዋሳ ከተማ የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ተካሂዷል፡፡

በመርሀግብሩ መሰረትም በወንዶች የ10 ሺህ ሜትር፤ በሴቶች ደግሞ የ5 ሺህ ሜትርና የሕፃናት ውድድሮች ተካሂደዋል፡፡


 

በውድድሩ ላይ የተገኙት የሲዳማ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶማርሶ ዶና በዓሉን ምክንያት በማድረግ በየዓመቱ የሚካሄደው ውድድር የፊቼ ጫምባላላን በዓል ከማድመቅ ባለፈ በውስጡ ያሉትን የአብሮነትና የሠላም እሴቶች ለማስተዋወቅና ለማጠናከር እያገዘ መሆኑን ተናግረዋል።

በዛሬው ስፖርታዊ ውድድርም ከክልሉና ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የመጡ አንጋፋና አዳዲስ አትሌቶች መሳተፋቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ይህም አዳዲሶቹ ከነባሮቹ ልምድ እንዲቀስሙ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ የአካባቢውን አትሌቲክስ ይበልጥ ለማነቃቃት ጠቃሚ መሆኑን አስረድተዋል።

ውድድሩን ያዘጋጀው የ“ብራይት አፍሪካ ራን” መስራችና ሥራ አስኪያጅ ካሳሁን ካቢሶ በበኩላቸው በዓሉን ምክንያት በማድረግ ውድድሩ ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ መካሄዱን ተናግረዋል።

በቀጣይ  ወደ ፕሮፌሽናል ውድድር እያደገ እንደሚሄድ ጠቁመው፣ ውድድሩ የ"ፊቼ ጫምባላላ" በዓልን ለዓለም በማሳየት ረገድ ጉልህ ድርሻ  እንዳለውና ዘንድሮም በተሳካ ድምቀት መከናወኑን ተናግረዋል፡፡

በሁለቱም ርቀት በተካሄዱ ውድድሮች አንደኛ የወጡ አትሌቶች የሜዳልያና የ30 ሺህ ብር ሽልማት ሲያገኙ እስከ 10ኛ ደረጃን የያዙትም የተለያየ መጠን ያለው ገንዘብና የሜዳሊያ ሽልማት እንደተበረከተላቸው ገልጸዋል።


 

በወንዶች 10 ሺህ ሜትር አንደኛ የወጣው አትሌት አብዱልመጂድ አባደላ ውድድሩን ቀዳሚ ሆኖ ማጠናቀቅ በመቻሉ ደስታ እንደተሰማው ተናግሯል፡፡

ውድድሩ ለበዓሉ ድምቀት የራሱን አስተዋጾ ማድረጉን ጠቅሶ፣ በውድድሩ ከተለያዩ አካባቢዎች ከመጡ አትሌቶችና ከሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ጋር መታደሙ ልዩ ስሜት እንደፈጠረለት ተናግሯል፡፡

የሀዋሳ አየርና ጎዳናው ለውድድሩ ምቹ እንደነበር የተናገረችው ደግሞ በሴቶች የ5 ሺህ ሜትር ውድድር አንደኛ የወጣችው አትሌት እመቤት ሽብሩ ናት፡፡


 

ውድድሩ ብቃቷን ለመገምገም ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላት ጠቁማ፣ እንዲህ ያሉ ውድድሮች ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት ሚናቸው የጎላ በመሆኑ መጠናከር አለባቸው ብላለች።

በጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር የሲዳማ ክልልና የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡    

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም