ቀጥታ፡

በክልሉ የመጣውን ሰላም ዘላቂ በማድረግ የህዝብን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው

ባሕርዳር፤ መጋቢት 5/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የመጣውን ሰላም ዘላቂ በማድረግ የህዝብን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የማህበራዊ ክላስተር ዘርፍ አስተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ(ዶ/ር) ገለጹ።

በባህር ዳር ከተማ ''ለሰላም ዘብ እንቆማለን፤ የልማት አርበኛ እንሆናለን'' በሚል መሪ ሀሳብ የተለያዩ የፌዴራል ተቋማት የስራ ኃላፊዎች የተገኙበት የምክክር መድረክ እየተካሔደ ነው።

በመድረኩ የተገኙት ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር)፤ በክልሉ የመጣውን ሰላም ዘላቂ በማድረግ የህዝብን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል።


 

በክልሉ ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሰው ተኮር የልማት ፕሮጀክቶች መገንባታቸውንና በሂደት ላይ ያሉ መኖራቸውን ጠቅሰው ለስኬቱ መትጋት ይጠበቅብናል ብለዋል።

የትኛውንም የፖለቲካ እሳቤ ይዞ የሚንቀሳቀስ አካል በሃሳብ የበላይነት አሸናፊ ለመሆን መስራት እንደሚጠበቅበት አንስተዋል።

ለዚህም የሀገራዊ ምክክሩን መልካም እድል በአግባቡ መጠቀም እንዲሁም ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ተሳትፎና ፉክክር በማድረግ ጠንካራ ሀገረ መንግስት መገንባት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

በዘንደሮው ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ፉክክር በማድረግ ኢትዮጵያን አሸናፊ ማድረግ ከሁሉም የፖለቲካ ተዋናዮች የሚጠበቅ መሆኑን አንስተዋል።

ጠቅላላ ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሐዊ፣ ዴሞክራሲያዊና የሁሉንም ተሳትፎ ያረጋገጠ እንዲሆን መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ገልጸው ለስኬቱ የሁሉም ቀና ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል።


 

የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ፤ የባህር ዳርን የተፈጥሮ ፀጋ በመግለጽና በማልማት ለኢንቨስትመንት፣ ለቱሪዝም ብሎም ለኑሮ የተመቸች ከተማ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

የልማት ስራዎቹ ይበልጥ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ሁሉም ለሰላም መቆም፣ የተሟላና ዘላቂ ሰላም ማስፈን የሁሉም ሃላፊነት ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በመሆኑም ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የሰላምን ዘላቂነት ማፅናት እንደሚገባ ጠቅሰው ለዚህም የልማት አርበኛ በመሆን በጋራ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም