በመዲናዋ ከነዳጅ ስርጭትና ግብይት ጋር የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በቅንጅት እየተሠራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ ከነዳጅ ስርጭትና ግብይት ጋር የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በቅንጅት እየተሠራ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 5/2018(ኢዜአ)፦ ከተማ አስተዳደሩ ከነዳጅ ስርጭትና ግብይት ጋር የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ መሆኑን የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ ገለፁ።
የአስተዳደሩ ንግድ ቢሮ ከነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ጋር በመተባበር በከተማዋ በሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቃኘት የተደረገ የመስክ ስራ ሪፖርት አስመልክቶ ከዘርፉ ተዋናዮች ጋር ውይይት እያካሄደ ነው።
በመድረኩ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ፣ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ሀቢባ ሲራጅ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ በከተማዋ የሚገኙ ነዳጅ ማደያዎች በህጋዊ ስርዓት ለተጠቃሚዎች ከማቅረብ አኳያ በአንዳንድ ማደያዎች ክፍተቶች መኖራቸውን ገልፀዋል።
ከሚታዩ ችግሮች መካከል የወሩ መጨረሻ አካባቢ በማደያዎች በቂ የነዳጅ ክምችት እያለ ለተሽከርካሪዎች የለም በማለት የሚመልሱ መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
ከተማ አስተዳደሩ በአንዳንድ ማደያዎች የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታትና አጥፊዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው ያሉት ከንቲባው በቀጣይም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የተጠናከረ እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል።
የንግድ ቢሮ ኃላፊ ሀቢባ ሲራጅ በበኩላቸው ከነዳጅ አቅርቦት ጋር በተገናኘ ያሉ ችግሮችን ለመለየትና የመፍትሔ አቅጣጫ ለማስቀመጥ በከተማዋ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች በሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች ላይ የክትትልና የቁጥጥር ስራ ተሰርቷል ብለዋል።
ከተለዩ ችግሮች መካከል የነዳጅ ቅሸባ፣ ማደያዎች በሙሉ አቅም 24 ሰዓት አገልግሎት አለመስጠት፣ ዘመናዊ የመለኪያ ማሽኖችን አለመጠቀም፣ ፍትሐዊ ያልሆነ የነዳጅ ስርጭት መኖር፣ አንዳንድ የነዳጅ ማደያዎች ነዳጅን በዲጂታል ክፍያ አለመሸጥ ተጠቃሽ መሆናቸውን አብራርተዋል።
በወሩ መጨረሻ የነዳጅ ዋጋ ይጨምራል በሚል ሰበብ የነዳጅ ቦቴ እንዲዘገይ የሚያደርጉ ማደያዎችና ኩባንያዎች መኖራቸው በክትትል መረጋገጡንም አንስተዋል።
ቢሮው በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ህግን ተከትለው የማይሰሩ አካላት ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ባለፉት ስድስት ወራትም ከህገ ወጥ የነዳጅ ዝውውር ጋር በተገናኘ 24 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ሰባቱ የፍርድ ውሳኔ እንደተላለፈባቸው ጠቁመዋል።