የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ለቀጣናው ሀገራት ትስስርና ተጠቃሚነት ጉልህ ሚና አለው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ለቀጣናው ሀገራት ትስስርና ተጠቃሚነት ጉልህ ሚና አለው
ሀዋሳ፤ መጋቢት 5/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ማግኘት ለአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የልማት ትስስርና ተጠቃሚነት ጉልህ ሚና እንዳለው ምሁራን ገለጹ።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት ምሁራን ኢትዮጵያ ለዘመናት ተነጥላ ከማታውቀው ቀይ ባህር የተገለለችው በሴራና በግፍ መሆኑን አስታውሰው ይህም ዛሬ ሀገርና ትውልድን ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል ብለዋል።
ያጣችውን የባህር በር ዓለም አቀፍ ህግ፣ መልክአ ምድራዊና ታሪካዊ መብቶችን ባከበረ መልኩ መልሳ ካገኘች ለቀጣናው ሀገራት የጋራ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑንም ተናግረዋል።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የእንግሊዝኛ ቋንቋና ስነጽሁፍ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ እንዳልካቸው ጀንበሬ (ዶ/ር) እንደገለጹት አትዮጵያ በሺህ ዘመናት ታሪኳ ከቀይ ባህር ተነጥላ ባታውቅም በሴራ ባለፉት 30 ዓመታት የባህር በር አጥታ ዋጋ እየከፈለች ነው።
ኢትዮጵያ ከባህር በር መገለሏ አሁን በአፍሪካ ቀንድና በቀይ ባህር አካባቢ ከሚታየው አለመረጋጋት በአንድም በሌላ መንገድ እንደሚገናኝ ገልጸው፣ ከዚህም የተነሳ ዓለም የኢትዮጵያን የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ እየደገፈው መምጣቱን ተናግረዋል።
በመካከለኛው አፍሪካ ኮንጎ ለሁለት ስትከፈል እንዲሁም በአውሮፓም ሀገራት ለሁለት ሲለያዩ የባህር በር ጉዳይ ታሳቢ መደረጉን ያስታወሱት እንዳልካቸው (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የሆነው ግን ከዚህ የተለየና አሳዛኝ በመሆኑ መታረም አለበት ብለዋል።
የአፍሪካ ሕብረት ሲመሰረት በኢኮኖሚ የተዋሃደ አፍሪካን የመፍጠር ግብን ለማሳካት እንደሆነ አስታውሰው፣ ሕብረቱ የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት መሆን ለቀጣናው ሀገራት ያለውን ጥቅም በመገንዘብ ድጋፉን ሊያጠናክር ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ነጻነትና ለህብረቱ መመስረት ፋና ወጊ ሀገር ናት ያሉት ደግሞ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና ተመራማሪ ንጉስ በላይ (ዶ/ር) ናቸው።
በአፍሪካ ሕብረት ዘንድ ተሰሚነት ያላት ኢትዮጵያ የባህር በር ሳይኖራት መኖር ለአፍሪካ ትስስርና ውህደት የሚኖረውን አሉታዊ ጎን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የህብረቱ መሪዎች እንዲያውቁት በግልጽ ማቅረባቸው ብልህነት የተሞላበት አካሄድና ትልቅ የዲፕሎማሲ ሲኬት መሆኑንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በአስተማማኝ መልኩ ምላሽ ማግኘት ለቀንዱ ሀገራትና ለመላው አፍሪካ የኢኮኖሚ ትስስር፣ ዕድገትና መረጋጋት ያለው ሚና የላቀ መሆኑንም ንጉስ (ዶ/ር) አስረድተዋል።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ምህረት ዳናንቶ (ዶ/ር) በበኩላቸው የባህር በር ማጣት ኢትዮጵያ ባላት ኢኮኖሚ ተጠቅማ የህዝቦቿን ፍላጎት በሚፈለገው መጠን ለማሟላት እንዳትችል እንቅፋት ሆኗል።
ሀገሪቱ በየዓመቱ ለጅቡቲ ወደብ ኪራይ የምታወጣው ገንዘብ በርካታ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን የሚያስችላትን ዕድል እያሳጣት መሆኑንም ነው የተናገሩት።
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ የወደብ ኪራይን ከማስቀረት ባለፈ የደህንነትና ብሔራዊ ጥቅም የማስከበር ጉዳይ በመሆኑ አፋጣኝ ምላሽ ይፈልጋል፤ ለዚህም ሁላችንም ልንተባበር ይገባል ብለዋል።
በቀይ ባህር አካባቢ ላለው የውሃ ኡደት ኢትዮጵያ በዓመት ከ122 ቢሊዮን በላይ ኪዩቢክ ውሃ እንደምታዋጣ ያነሱት ምህረት (ዶ/ር)፣ በዚህ መጠን አስተዋጽኦ ያላት ሀገር ከቀይ ባህር መገለሏ ተገቢነት የለውም ብለዋል።
ለቀጠናውም ሆነ ለመላ አፍሪካ ሰላምና ትስስር መጠናከር የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ ወሳኝ በመሆኑ ነባራዊ ሁኔታው ታይቶ ተገቢ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።
ምሁራኑ እንዳሉት የኢትዮጵያ ህዝብ ከ130 ሚሊዮን በላይ በደረሰበት በዚህ ወቅት በርካታ ቢሊዮኖችን ለወደብ ኪራይ ማውጣት ኢኮኖሚያዋን ከመጉዳት ባለፈ ለቀጣናዊ ዕድገትና መረጋጋት የሚኖረው ተጽዕኖ ቀላል እንዳልሆነም ሊጤን ይገባል ብለዋል።