የፋይዳ የመመዝገብ አቅምን የሚያሳድጉ ሶስት ሺህ አዳዲስ መመዝገቢያ መሳሪያዎች ወደ ሥራ ሊገቡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የፋይዳ የመመዝገብ አቅምን የሚያሳድጉ ሶስት ሺህ አዳዲስ መመዝገቢያ መሳሪያዎች ወደ ሥራ ሊገቡ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 5/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ የመመዝገብ አቅምን የሚያሳድጉ ሶስት ሺህ አዳዲስ መመዝገቢያ መሳሪያዎችን (ባዮሜትሪክ ኪቶች) በቅርቡ ወደ ሥራ ለማስገባት ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም አስታወቀ።
እስከ አሁን የፋይዳ ብሄራዊ መታወቂያ ተመዝጋቢዎች ቁጥር 38 ሚሊየን መድረሱም ተገልጿል።
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የባለድርሻ አካላትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሳሚናስ ሰይፉ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት በሀገር አቀፍ ደረጃ ሰባት ሺህ መመዝገቢያ መሳሪያዎች አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።
የምዝገባ ሂደቱን ይበልጥ ለማቀላጠፍም ተጨማሪ ሶስት ሺህ የባዮሜትሪክስ ኪቶች ተገዝተው ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከመካከለኛው ሲስተም ጋር የማናበብ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
እነዚህ መሳሪያዎች ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገቡ የምዝገባ አቅምን እንደሚያሳድጉ ጠቁመው፤ በአሁኑ ወቅት በሳምንት እስከ አንድ ሚሊየን ዜጎችን መመዝገብ የሚያስችል አቅም መፈጠሩንም አክለዋል።
እስከአሁን ባለው ሂደት የፋይዳ ብሄራዊ መታወቂያ ተመዝጋቢዎች ቁጥር 38 ሚሊየን መድረሱን አስታውቀዋል፡፡
ዜጎች ለምዝገባ በሚመጡበት ወቅት በጣም ባጠረ ጊዜ የፋይዳ መለያ ቁጥራቸው በእጅ ስልካቸው እንዲደርሳቸው እየተደረገ ያለው ጥረት ውጤታማ መሆኑን ጨምረው ጠቅሰዋል።
ምዝገባው በስፋት ተደራሽ እንዲሆን ከባንኮች፣ በኢትዮ-ቴሌኮም ቅርንጫፎች፣ በኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት እንዲሁም ከሌሎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የዲጂታል ሥርዓቱን ከተለያዩ ተቋማት ጋር የማስተሳሰር ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቅሰው፤ ከባንኮች፣ ከወሳኝ ኩነት ምዝገባ እና ከትምህርት ተቋማት ጋር የማስተሳሰር ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
በተለይም ህጻናት በትምህርትና በጤና የተሳለጠ አገልግሎት እንዲያገኙ የፋይዳ መታወቂያ እንዲመዘገቡ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ፋይዳን ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ያስገቡ ተቋማት አገልግሎታቸውን ማዘመን መቻላቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ በፋይናንስ ተቋማት ላይ የሚስተዋሉ የማጭበርበር ሙከራዎችን በመከላከል በኩል ከፍተኛ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡
በተጨማሪም የባንክ ተጠቃሚዎች በፋይዳ አማካኝነት የብድር አገልግሎት የሚያገኙበት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንና ተቋማት የደንበኞቻቸውን ማንነት በአስተማማኝ ሁኔታ በማረጋገጥ አገልግሎታቸውን እንዲያዘምኑ ማስቻሉንም ገልጸዋል፡፡
ከፋይዳ ዋና ዋና ዓላማዎችና ጥቅሞች መካከል ዲጂታል ኢኮኖሚን መገንባት፣ የአገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን፣ ደህንነትና አመኔታ፣ የፋይናንስ አካታችነት እና ሌሎችም ተጠቃሽ ናቸው፡፡