የህዝብን ሰላምና አብሮነት ለማጎልበት ከሃይማኖት ተቋማት ጋር በትብብር የሚሰሩ ሥራዎች ይጠናከራሉ - ኢዜአ አማርኛ
የህዝብን ሰላምና አብሮነት ለማጎልበት ከሃይማኖት ተቋማት ጋር በትብብር የሚሰሩ ሥራዎች ይጠናከራሉ
ሆሳዕና፤ መጋቢት 5/2018(ኢዜአ)፦ የህዝብን ሰላምና አብሮነት ለማጎልበት ከሃይማኖት ተቋማት ጋር በትብብር የሚሰሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር) ገለጹ።
"በመደመር መንግሥት እይታ የኃይማኖት ተቋማት ሚና" በሚል መሪ ሀሳብ ከካቶሊክ ሀይማኖት አባቶችና ምዕመናን ጋር የተዘጋጀ ክልል አቀፍ የምክክር መድረክ በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት በክልሉ ከኃይማኖት ተቋማት ጋር በትብብር በመስራት የህዝብን አብሮነትና የሰላም ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተጀመሩ ተግባራት ይጠናከራሉ።
ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥና የህዝብን የልማት ተጠቃሚነት ለማሳደግ መንግስት እየተጋ መሆኑን ጠቁመው ሰላምና ልማትን ለማስቀጠል በሚሰሩ ሥራዎች የሃይማኖት ተቋማይ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለሀገር ሉአላዊነት መጠበቅ በቀደምት ጀግኖች አርበኞች የተከፈለው ዋጋ ቀላል እንዳልሆነ አስታውሰው፣ የአሁኑ ተውልድም ድህነትን በማሸነፍ ለተተኪው ትውልድ የበለጸገች ሀገር በማስረከብ የራሱን አሻራ ማኖር አለበት ብለዋል።
ለዚህም በስነምግባርና በአብሮነት የታነጸ ዜጋ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፣ በዚህ ረገድ ከሀይማኖት ተቋማት ጋር በትብብር የሚሰሩ ሥራዎች ይጠናከራሉ ሲሉ ገልጸዋል።
ቤተክርስቲያኗም በሥነ ምግባር የታነጸ፣ ብቁና ክህሎት ያለው ዜጋ የማፍራት ሚናዋን አጠናክራ መቀጠል እንዳለባት አስገንዝበዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት ከቤተ ክርስቲያኗ ጋር በሰላም ማስጠበቅና ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎች ላይ በትብብር የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ተመስገን ካሳ በበኩላቸው የኃይማኖት ተቋማት ለዘላቂ ሰላም መጠበቅና ለዜጎች አብሮነት መጠናከር ሲያበረክቱት የነበረውን አስተዋጽኦ ማጠናከር አለባቸው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በክልሉ ሰላምን ከማጽናት ጎን ለጎን የህዝብ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ በርካታ የልማት ሥራዎችን እያከናወነች መሆኗንም አንስተዋል።
በተለይ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች በልማት ሥራ፣ በሰላም ግንባታና አብሮነትን በማጠናከር በኩል ያከናወነቻቸውን ተግባራት በቀጣይም አጠናክራ ልታስቀጥል ይገባል ነው ያሉት።
በመርሐ ግብሩ የቤተ ክርስቲያኗ አባቶች፣ ምዕመናንና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በመሳተፍ ላይ ናቸው።