ቀጥታ፡

ምርጫው የሀገርና የህዝብን ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ በስኬት እንዲጠናቀቅ በትብብር እየሰራን ነው − የፖለቲካ ፓርቲዎች

ዲላ፤ መጋቢት 5/2018 (ኢዜአ)፡-7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሀገርና የህዝብን ጥቅም ባስቀደመ መልኩ በስኬት እንዲጠናቀቅ በትብብር እየሰሩ መሆናቸውን በጌዴኦ ዞን የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።

በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መርሀግብር መሰረት የፖለቲካ ፓርቲዎቹ እጩዎቻቸውን ከማስመዝገብ ባለፈ የምርጫ ፕሮግራምና ማኒፌስቷቸውን ለህዝብ እያስተዋወቁ ይገኛሉ።  

የጌዴኦ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ዋና ጸሐፊ ግርማ ሐጌ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በምርጫው በነጻነት ለመወዳደር የሚያስችል ሰፊ ምህዳርና ፉክክር ለማድረግ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል።

በተለይ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ከጥሎ ማለፍ የፖለቲካ ፉክክር በመውጣት ሀገርን ለሚያሻግር ሀሳብና አተያይ ይበልጥ ትኩረት መደረጉን ጠቅሰው ይህም ኢትዮጵያን ለማጽናት ትልቅ እገዛ ይኖረዋል ብለዋል።

ፓርቲው በምርጫው ተወዳድሮ አሸናፊ ለመሆን እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለእዚህም የፓርቲውን የልማትና የመልካም አስተዳደር አማራጭ ሀሳቦች ለህዝብ በማቅረብ በሃሳብ የበላይነት ብቻ ለማሸነፍ በሰላማዊ መንገድ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ብለዋል።

በእስካሁኑ የምርጫ ሂደት እጩዎቻቸውን ከማቅረብ ባለፈ የሀሳብ የበላይነት ለመያዝ የሚያስችል ጠንካራ ፉክክር እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

ምርጫው ተአማኒ፣ ነጻና በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ከማድረግ ባለፈ ዴሚክራሲያዊ ሥርአትን በሚያጎለብት መልኩ እንዲካሄድ ፓርቲው የበኩሉን እንደሚወጣም አረጋግጠዋል።  

7ኛ ጠቅላላ ምርጫ የሀገርና የህዝብን ክብር ባስቀደመ መልኩ እንዲጠናቀቅ በቁርጠኝነት እየሰሩ መሆኑ ያነሱት ደግሞ የጌዴኦ ዞን ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጸሐፊና የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ የዞኑ ሰብሳቢ አቶ ተፈራ ጎበና ናቸው።

ሰባተኛው ምርጫ የህዝብ ድምጽ የሚከበርበትና የሃሳብ የበላይነት ብቻ አሸንፎ ተቀባይነትን የሚያገኝበት ሆኖ እንዲጠናቀቅ በጋራ ምክር ቤቱ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በምርጫው አሸናፊ ለመሆን ጠንካራ ፉክክር ማድረግ እንደሚገባ ገልጸው፣ ምርጫው ሀገርን ያስቀደመና የህዝብን ድምጽ ያከበረ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የጋራ ምክር ቤቱ የበኩሉን እንደሚወጣ አረጋግጥዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የጌዴኦ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካና የህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ሃላፊ አቶ አዲሱ አየለ በበኩላቸው እንዳሉት ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍጹም ሰላማዊ፣ ዴሞክራዊያዊና ተአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እየተሰራ ነው።

ምርጫው የተለያዩ ፓርቲዎች አማራጭ ሀሳብ በስፋት የሚንሸራሸርበት፣ የሀሳብ የበላይነት የሰፈነበትና ሀገር የምታሸንፍበት እንዲሆን ከፓርቲዎች ጋር በትብብር እየሰራን ነው ብለዋል።

በተለይ የምርጫ ህጉን አክብሮ ከመንቀሳቀስ ባለፈ ህዝቡ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ መሰረት የመራጭነት ካርድ እንዲወስድ ቅስቀሳ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም