በፕሪሚየር ሊጉ አርሰናል ከኤቨርተን ማንችስተር ሲቲ ከዌስትሃም ዩናይትድ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ይጠበቃሉ - ኢዜአ አማርኛ
በፕሪሚየር ሊጉ አርሰናል ከኤቨርተን ማንችስተር ሲቲ ከዌስትሃም ዩናይትድ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ይጠበቃሉ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 5/2018 (ኢዜአ)፦ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 30ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል።
በዕለቱ አምስት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።
ምሽት 2 ሰዓት ከ30 ላይ አርሰናል ኤቨርተንን በኤምሬትስ ስታዲየም ያስተናግዳል።
አርሰናል በ67 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው። ኤቨርተን በ43 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃን ይዟል።
ጨዋታው አርሰናል የሊጉን መሪነት ለማጠናከር፣ ኤቨርተን ሶስተኛ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ የሚያደርጉት ነው።
የ42 ዓመቱ አንዲ ማድሊ ጨዋታውን በዋና ዳኝነት ይመሩታል።
በሌላኛው መርሐ-ግብር ዌስትሃም ዩናይትድ ከማንችስተር ሲቲ ምሽት አምስት ሰዓት ላይ በለንደን ስታዲየም ይጫወታሉ።
ዌስትሃም ዩናይትድ በ28 ነጥብ 18ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ማንችስተር ሲቲ በ60 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ዌስትሃም ዩናይትድ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት በሚያደርገው ትግል ሶስት ነጥብ ማግኘት ወሳኝ ነው።
ማንችስተር ሲቲ በዋንጫው ፉክክር ለመቆየት ጨዋታውን ማሸነፍ ይጠበቅበታል።
የ41 ዓመቱ ማይክል ኦሊቨር የጨዋታው መሐል ዳኛ ናቸው።
ቼልሲ ከኒውካስትል ዩናይትድ ምሽት 2 ሰዓት ከ30 ላይ በስታምፎርድ ብሪጅ ስታዲየም ይጫወታሉ።
የምዕራብ ለንደኑ ቼልሲ በ48 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል። ኒውካስትል ዩናይትድ በ39 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ቼልሲ የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ ውጥኑን ለማስቀጠል፣ ኒውካስትል ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይጫወታሉ።
በርንሌይ ከቦርንማውዝ እና ሰንደርላንድ ከብራይተን በተመሳሳይ ምሽት 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።