ሃዋሳ ከተማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ተጠባቂ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሃዋሳ ከተማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ተጠባቂ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 5/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 24ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።’
ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሃዋሳ ከተማ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በውድድር ዓመቱ እስከ አሁን ባደረጋቸው 23 ጨዋታዎች ስድስቱን ሲያሸንፍ ስምንት ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ ዘጠኝ ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። በጨዋታዎቹ ላይ 28 ግቦችን ሲያስቆጥር 30 ግቦችን አስተናግዷል።
የ2016 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ27 ነጥብ 13ኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው ሃዋሳ ከተማ በሊጉ ባከናወናቸው 23 ጨዋታዎች በ11ዱ ድል ሲቀናው በአምስት ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግዷል። በሰባት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። 26 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 14 ጎሎች ተቆጥረውበታል።
ሃዋሳ ከተማ በ42 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።
ሁለቱም ቡድኖች ተከታታይ ድላቸውን ለማስመዝገብ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።
ሃዋሳ ከተማ ካሸነፈ ከሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሁለት ዝቅ ያደርጋል።
በተያያዘም በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም አርባምንጭ ከተማ ከኢትዮጵያ መድን ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
አርባምንጭ ከተማ በሊጉ ካደረጋቸው 23 ጨዋታዎች መካከል ማሸነፍ የቻለው ሶስት ጊዜ ብቻ ነው። 10 ጊዜ ሲሸነፍ በተመሳሳይ 10 ጨዋታዎች አቻ ወጥቷል። በ23 ጨዋታዎች 16 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 27 ጎሎችን አስተናግዷል።
ቡድኑ በ19 ነጥብ የመጨረሻውን 20ኛ ደረጃ ይዟል።
የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ መድን ካደረጋቸው ጨዋታዎች በአምስቱ ድል ሲቀናው ስምንት ጊዜ ተሸንፏል። 10 ጊዜ አቻ ወጥቷል። 17 ግቦችን ሲያስቆጥር በተመሳሳይ 18 ጎሎች ተቆጥረውበታል።
መድን በ25 ነጥብ 16ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
አርባምንጭ ከተማ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይጫወታል። ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አቻ የወጣው ኢትዮጵያ መድን ማሸነፍ ወደ ድል መንገድ ይመልሰዋል።
ኢትዮጵያ ቡና ከአዳማ ከተማ ምሽት 12 ሰዓት ላይ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ቡናማዎቹ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀራቸው በ29 ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዘዋል። አዳማ ከተማ በ33 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ሁለቱም ቡድኖች በ23ኛ ሳምንት ካስተናገዱት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታሉ።
በሌላኛው መርሐ-ግብር ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከድሬዳዋ ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በ25 ነጥብ 18ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። ድሬዳዋ ከተማ በ28 ነጥብ 12ኛ ደረጃን ይዟል።
በ23ኛ ሳምንት ወልዋሎ ከመቻል ጋር ያለ ግብ አቻ ሲለያይ ድሬዳዋ ከተማ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ2 ለ 1 ሽንፈት አስተናግዷል።
ሁለቱም ቡድኖች ወደ አሸናፊነት መንገድ ለመመለስ ይጫወታሉ።