የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ በኔዘርላንድስ እና ኢትዮጵያ መካከል የተሻለ የንግድ ትብብር ለመፍጠር መሰረት የሚጥል ነው - አምባሳደር ክርስቲን ፓይሪን - ኢዜአ አማርኛ
የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ በኔዘርላንድስ እና ኢትዮጵያ መካከል የተሻለ የንግድ ትብብር ለመፍጠር መሰረት የሚጥል ነው - አምባሳደር ክርስቲን ፓይሪን
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 4/2018(ኢዜአ)፦ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ በኔዘርላንድስ እና ኢትዮጵያ መካከል ያለውን የንግድ ትስስር ለማጠናከር ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን በኢትዮጵያ የኔዘርላንድስ አምባሳደር ክርስቲን ፓይሪን ገለጹ።
ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም እየተገበረች ትገኛለች።
ሪፎርሙ የማክሮ ኢኮኖሚ ሚዛንን መጠበቅ፣ የዋጋ ንረትን መቆጣጠር፣ የተለያዩ ዘርፎችን ለውጭ ኢንቨስትሮች ክፍት ማድረግ፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን መሳብ፣ የወጪ ንግድ ገቢን ማሳደግ እንዲሁም ጥራት ያለው እና የግሉ ዘርፍ የሚመራው ሁሉን አቀፍ እድገት ማምጣትን ያለመ ነው።
በኢትዮጵያ የኔዘርላንድስ አምባሳደር ክርስቲን ፓይሪን ኢትዮጵያ በማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ የወሰደቻቸው ጠንካራ እርምጃዎች በሁለቱ ሀገራት መካከል የተሻለ የንግድ ግንኙነት ለመፍጠር መሰረት የጣለ መሆኑን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።
ሪፎርሙ የንግድ ስራ ምቹነትን በማሻሻል የንግድ ልውውጥ መጠንን ለማሳደግ ቁልፍ ሚና እንዳለውም አመልክተዋል።
ሀገራቱ 100 ዓመታትን ያስቆጠረ የዲፕሎማሲና የንግድ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቅሰው የኔዘርላንድስ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ያላቸውን የንግድ እና የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ከሁለትዮሽ ትብብሩ ዋና የትኩረት መስኮች መካከል አንዱ ነው ብለዋል።
ግብርና፣ ውሃ፣ ምግብ፣ ስርዓተ ምግብ እና ጤና ሀገራቱ በትብብር ከሚሰሩባቸው መስኮች መካከል እንደሚጠቀሱ ገልጸዋል።
ኔዘርላንድስ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን አንድ ክፍለ ዘመን ገደማ ያስቆጠረ የረጅም ጊዜ ትብብር ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗንም ነው አምባሳደሯ ያረጋገጡት።
ኢትዮጵያ እና ኔዘርላንድስ ዲፕሎማሲያዊ ትብብር የጀመሩበትን 100ኛ ዓመት እ.አ.አ አፕሪል 2026 ያከብራሉ።
እ.አ.አ በ1926 የተጀመረው የዲፕሎማሲ ግንኙነት ማሳያ አንዱ ንግድ ሲሆን ሁለቱ ሀገራት የንግድ፣ ኢንቨስትመንት እና የልማት ትብብራቸውን ለማጠናከር እየሰሩ ይገኛሉ።
ከ100 በላይ የኔዘርላንድስ ኩባንያዎች ግብርናን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ተሰማርተው እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።