ቀጥታ፡

ሲዳማ ቡና ምድረ ገነት ሽሬን በማሸነፍ መሪነቱን አጠናከረ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 4/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 24ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ሲዳማ ቡና ምድረ ገነት ሽሬን 2 ለ 0 አሸንፏል።

ማምሻውን በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው  ጨዋታ ብርሃኑ በቀለ እና አዲስ ፈራሚው አቤል ያለው ግቦቹን አስቆጥረዋል።

ሲዳማ ቡና ነጥቡን ወደ 45 ከፍ በማድረግ መሪነቱን አጠናክሯል። ከተከታዩ ሃዋሳ ከተማ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አምስት ከፍ አድርጓል። 

በውድድር ዓመቱ 12ኛ ድሉንም አስመዝግቧል።

በአንጻሩ በሊጉ ስምንተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ምድረ ገነት ሽሬ በ27 ነጥብ 14ተኛ ደረጃን ይዟል። ቡድኑ ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች አላሸነፈም። 

በዝውውር መስኮቱ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ሲዳማ ቡና ያመራው አቤል ያለው በውድድር ዓመቱ ያስቆጠራቸውን ጎሎች ብዛት ወደ 10 ከፍ በማድረግ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን መምራት ጀምሯል። 

ለሲዳማ ቡና በሁለት ጨዋታዎች ሁለት ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፏል።

በሌላኛው መርሐ-ግብር  ባህርዳር ከተማ  ቅዱስ ጊዮርጊስን 2 ለ 0 አሸንፏል።

በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ አንተነህ ተፈራ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥሯል።

ከሶስት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት የተመለሰው ባህር ዳር ከተማ በ31 ነጥብ ደረጃውን ከ10ኛ ወደ 8ኛ ከፍ አድርጓል። በሊጉ ስድስተኛ ድሉን አስመዝግቧል።

በውድድር ዓመቱ 10ኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ25 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

ቡድኑ ባለፉት ስምንት የሊግ ጨዋታዎች አላሸነፈም።

ዛሬ ቀን ላይ በተደረጉ የ24ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች ሸገር ከተማ ሀዲያ ሆሳዕናን 2 ለ 0 ሲያሸንፍ ፋሲል ከነማ እና መቻል ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም