ማህበሩ በጋሞ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተፈናቀሉ ወገኖች የምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ማህበሩ በጋሞ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተፈናቀሉ ወገኖች የምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ
አርባምንጭ፤ መጋቢት 4/2018 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በጋሞ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ6 ሚሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።
የቅርንጫፉ ሃላፊ ተስፋዬ ዱንዳ እንደገለጹት ድጋፉ በአደጋው ለተፈናቀሉ ወገኖች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የተደረገ ነው።
ድጋፉ ባለሀብቶችን ጭምር በማስተባበር የተደረገ መሆኑን ጠቁመው ለሁለተኛ ጊዜ የተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
አደጋው ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ በመጀመሪያ ዙር ምግብ ነክ ያልሆነ ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን ጠቁመው የዛሬው ድጋፍም ምግብና ምግብ ነክ ያልሆነ ቁሳቁስ ያካተተ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ደምስ አድማሱ (ዶ/ር) መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ባለሀብቶች ለተጎጂዎች እያደረጉ ስላለው ማጽናናት እና ድጋፍ በዞኑ ህዝብ ስም አመስግነዋል።
የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም ግብረ ሃይል ተቋቁሞ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።