ለ"ፊቼ ጫምባላላ" በዓል የባህል አልባሳት በተመጣጣኝ ዋጋ ቀርበዋል--በሀዋሳ ሻጮችና ሸማቾች - ኢዜአ አማርኛ
ለ"ፊቼ ጫምባላላ" በዓል የባህል አልባሳት በተመጣጣኝ ዋጋ ቀርበዋል--በሀዋሳ ሻጮችና ሸማቾች
ሀዋሳ፤ መጋቢት 4/2018 (ኢዜአ)፡- ለሲዳማ ዘመን መለወጫ "ፊቼ ጫምባላላ" በዓል የባህል አልባሳት በተሻለ አማራጭና በተመጣጣኝ ዋጋ መቅረባቸውን በሀዋሳ ከተማ ሻጮችና ሸማቾች ተናገሩ፡፡
የዘንድሮው የሲዳማ የዘመን መለወጫ "ፊቼ ጫምባላላ" በዓል መጋቢት 5 እና 6 ቀን 2018 ዓ.ም በሃዋሰ ከተማ በድምቀት ይከበራል፡፡
በዩኔስኮ ከማይዳሰሱ ወካይ ቅርሶች አንዱ የሆነው "ፊቼ ጫምባላላ" በዓል በርካታ ህዝብ ታድሞበት በማይረሱና መሳጭ በሆኑ የተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች ታጅቦ ነው የሚከበረው።
በሀዋሳ ከተማም በባህል አልባሳት ገበያ በተለያየ የዲዛይን አማራጮች የቀረቡ አልባሳትም ለዋዜማው ልዩ ድምቀት ሆነዋል፡፡
በገበያው በመዘዋወር ኢዜአ ያነጋገራቸው የባህል አልባሳት ሻጮችና ሸማቾች ለበዓሉ በተሻለ የዲዛይን አማራጭ የቀረቡ አልባሳት በተመጣጣኝ ዋጋ እየተሸጡ መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡
የ"ቤተሰብ የባህል አልባሳት ማምረቻና መሸጫ" ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ መቅደስ አስፋው የባህል አልባሳት ገበያ ዓመቱን ሙሉ ያለ ቢሆንም በ"ፊቼ ጫምባላላ" በዓል ከወትሮው በተለየ መልኩ ይቀርባል ብለዋል።
ለበዓሉ ለሁሉም ሰው በሚመች መልኩ በተለያዩ ዲዛይኖች አልባሳትን አዘጋጅተው ማቅረባቸውን ጠቅሰው፣ አልባሳቱ የሸማቹን ኪስ በማይጎዳ መልኩ በተመጣጣኝ ዋጋ እየተሸጡ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
ከሀዋሳ ከተማ እንዲሁም ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የመጡ እንግዶች በዓሉን ለማድመቅ የባህል አልባሳት መግዛታቸውንም ጠቁመዋል፡፡
የ"ራማ የባህል አልባሳት ማምረቻና መሸጫ"ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ራሄል አበበ በበኩላቸው የባህል አልባሳቱን በሁሉም ዕድሜ ክልል ላሉ ለባሾች በሚመች መልኩ አዘጋጅተው ማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡
ዋጋቸው ተመጣጣኝ መሆኑን ጠቅሰው አልባሳቱ ከበዓሉ ውጪም ባሉ ቀናትም እንዲለበሱ በልዩ ዲዛይን ማዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል።
በዓሉን በድምቅት ለማሳለፍ በመረጠችው ዲዛይን የባህል ልብስ ማሰፋቷን የተናገረችው ወጣት አንቺንአየሁ ገብሬ በበኩሏ በከተማው በተለያዩ ፋሽን ዲዛይኖች የተዘጋጁ አላባሳትን መመልከቷን ገልጻለች።
ይህም በዓሉ ከዋዜማው ጀምሮ የተለየ ድምቀትና ድባብ እንዲላበስ ማድረጉን ተናግራ፣ የአልባሳቱም ዋጋ ተመጣጣኝ መሆኑን ተናግራለች፡፡
"ፊቼ ጫምባላላ" የአደባባይ በዓል እንደመሆኑ መጠን ያሉንን ውብ ባህሎች፣ አልባሳትና አብሮነታችንን ለዓለም የምናሳይበት ነው ስትልም ገልጻለች።
በተሻለ አማራጭ ከቀረቡ የባህል አልባሳት መካከል የፈለጉትን መርጠው ለመግዛት ከሆኮ ወረዳ ወደ ሀዋሳ ከተማ እንደመጡ የገለጹት ሌላው ሸማች ደግሞ አቶ ባጢሶ ዎጤ ናቸው።
ለርሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው የሚሆኑ የባህል አልባሳትን መሸመታቸውን ተናግረው፣ በባህል አልባሳት ገበያ የፈለጉትን ልብስ ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ መግዛታቸውን ተናግረዋል።
በዓሉን ከቤተሰብ እንዲሁም በአካባቢያቸው ካሉ ሰዎች ጋር በአብሮነትና በድምቀት ለማሳለፍ መዘጋጀታቸውንም ገልፀዋል፡፡