የኢትዮጵያ አፈፃፀም ክትትል ለትግበራ የጥናት ፕሮጀክት የጤና አገልግሎት ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ምቹ መደላድል ይፈጥራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አፈፃፀም ክትትል ለትግበራ የጥናት ፕሮጀክት የጤና አገልግሎት ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ምቹ መደላድል ይፈጥራል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 4/2018(ኢዜአ)፦ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው የኢትዮጵያ አፈፃፀም ክትትል ለትግበራ የጥናት ፕሮጀክት የሚሰበስባቸው መረጃዎች የዜጎችን የጤና አገልግሎት ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማሳደግ ምቹ መደላድል እንደሚፈጥሩ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ድጉማ ገለፁ።
ጤና ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የቀረጸው የዚሁ ሀገር አቀፍ የጥናት ፕሮጀክት የመስክ ሥራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በዛሬው ዕለት ተካሂዷል።
ጥናቱ ይፋ በተደረገበት ወቅት ዶክተር ደረጄ ድጉማ እንደገለጹት፤ መንግስት መረጃን መሠረት ያደረገ የውሳኔ አሰጣጥ ሥርዓትን ለመገንባት በትኩረት እየሰራ ይገኛል።
ለዚህም በየወሩ ከጤና ተቋማት የሚሰበሰቡ ሪፖርቶችና በየጊዜው የሚከናወኑ ጥናትና ምርምሮች እንደ ዋና የመረጃ ምንጭ ያገለግላሉ ብለዋል።
ይህ አዲስ የጥናት ፕሮጀክትም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ስትራቴጂካዊ ዕቅዶችን ሲያወጣና አዳዲስ ፖሊሲዎችን ወደ ተግባር ሲቀይር እንደ ትልቅ ግብዓት የሚያገለግል መሆኑን ጠቁመዋል።
የዳሰሳ ጥናቱ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ጠቁመው የአገልግሎቱን ተደራሽነትና ጥራት ማረጋገጥ፣ የእናቶችንና የሕፃናትን የጤና ክብካቤ ጥራት ማሻሻል እንዲሁም በአገር አቀፍ ደረጃ ያለውን ተጨባጭ የክትባት ሽፋን በማወቅ ለቀጣይ ፖሊሲዎች እንደ ግብዓት መጠቀም ዋነኞቹ ናቸው ብለዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት የጤና ተቋማትን በማስፋፋትና ግብዓቶችን በማሟላት የእናቶችና ሕፃናትን ጤና ከማስጠበቅ አንጻር ውጤታማ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቁመዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት ዲን ዶክተር ሙሉጌታ ታምሬ በበኩላቸው፤ ጥናቱ ሁሉንም የአገሪቱ ክልሎች የሚያካትት መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ የጥናት ፕሮጀክት ለአምስት ዓመታት የሚቆይ መሆኑን ጠቅሰው ከዓላማዎቹ መካከልም በአገር አቀፍ ደረጃ የተደራጀና ወቅታዊ መረጃ ማቅረብ፣ የጤናውን ዘርፍ ውጤታማነት ማረጋገጥ እና በዘርፉ የልህቀት ማዕከል ለመገንባት ማገዝ ናቸው ብለዋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ እናቶችና ህፃናት ስርዓተ ምግብ ዳይሬክተር መሪሁን ገብረ በሰጡት አስተያየት፤ እስካሁን በእናቶችና ሕፃናት ሞት ቅነሳ ዙሪያ የተመዘገቡ ውጤቶች የሚበረታቱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ማአከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ እናቶችና ህፃናት ስርአተ ምግብ ዳይሬክቶሬት አስተባባሪ ሙራድ መልስ በበኩላቸው ይህ አዲስ ጥናት መረጃን መሠረት ያደረገ ውሳኔ ለመስጠትና የታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አረጋግጠዋል።