የኢትዮጵያን ዕድገት የሚያፋጥን በዕውቀትና ክህሎት የበለጸገ የልማት አርበኛ ትውልድ ማፍራት እየተቻለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ዕድገት የሚያፋጥን በዕውቀትና ክህሎት የበለጸገ የልማት አርበኛ ትውልድ ማፍራት እየተቻለ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 4/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ የዕድገት ጉዞ የሚያፋጥን በዕውቀትና ክህሎት የበለጸገ የልማት አርበኛ ትውልድ ማፍራት እየተቻለ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ(ዶ/ር) ገለጹ።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ''ሙያ፣ ክህሎትና አርበኝነት፤ ትናንት፣ ዛሬና ነገ’’ በሚል መሪ ሃሳብ የባለድርሻ አካላት ውይይት አካሂዷል።
የመድረኩ ዓላማም ታሪካዊ ዕሴትን ከዘመናዊ አርበኝነት ጋር ማዛመድ፣ ተቋማዊ ስኬቶችን ማስቀጠል፣ የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ማጎልበትና የሙያ ክህሎትን ማዳበር ላይ ትኩረት አድርጓል።
በመድረኩ የኢትዮጵያ አርበኞች ማኅበር፣ የታሪክ ምሁራን፣ የኪነ-ጥበብና የሚዲያ ባለሙያዎች፣ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እና የተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ(ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት የሚያሳልጥ በክህሎት የበለጸገ ትውልድ ማፍራት የዘመኑ አርበኝነት ነው ብለዋል።
ከሶስት ዓመታት በፊት ተቀርጸው ተግባራዊ የተደረጉ ሥርዓተ ትምህርትና ስልጠና ስራዎች በዕውቀትና ክህሎት የበለጸገ የልማት አርበኛ ትውልድ ማፍራት እያስቻሉ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም ኢትዮጵያውያን በዕውቀትና ክህሎት መር አርበኝነትን በመታጠቅ በሁሉም መስክ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል።
የኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ መጻኢ እጣ ፋንታ ብሩህ ነው ብለዋል።
ለዚህም የነገዋን ኢትዮጵያ በተሻለ የልማት አርበኝነት ዓለምአቀፍ የዕድገት ተወዳዳሪነትን የሚያሳልጥ በዕውቀትና ክህሎት የበለጸገ ዜጋ የማፍራት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በቴክኒክና ሙያ ስልጠና የሚሰጡ የትምህርት ሥርዓቶችም ሀገር ወዳድነትን ከልማት አርበኝነትና ዘመናዊ ዓለም የዕውቀትና ክህሎት ጋር ተሰናስለው እየተተገበሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው በበኩላቸው፤ በዕውቀትና ክህሎት የበለጸገ ዜጋ የኢትዮጵያን ዕድገት የሚያሳልጥ የዘመኑ አርበኛ ነው ብለዋል።
በቀጣይም በሁሉም ዘርፍ የኢትዮጵያን ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪነት የሚያፋጥንና በሀገር ብሔራዊ ጥቅም ላይ በታላቅ ኃላፊነት የሚተጋ ትውልድ ማፍራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡