ቀጥታ፡

በጋሞ ዞን በመሬት ናዳ አደጋ የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመደገፍና መልሶ ለማቋቋም በቅንጅት እየተሰራ ነው

አርባ ምንጭ፤ መጋቢት 4/2018(ኢዜአ)፦ በጋሞ ዞን በመሬት ናዳ አደጋ የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመደገፍና መልሶ ለማቋቋም ከፌደራል መንግስት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ አስታወቁ።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ እና የክልሉና የጋሞ ዞን የሥራ ሃላፊዎች በዞኑ አደጋው በተከሰተበት ጋጮ ባባ ወረዳ ማዞ ዶይሳ ቀበሌ በመገኘት ተጎጂ ወገኖችን አጽናንተዋል።


 

በአደጋው የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋምና ወደነበሩበት ህይወት ለመመለስ የክልሉ መንግስት ከፌደራል መንግስት ጋር በመቀናጀት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በእስካሁንም በአደጋው ሳቢያ ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስና መልሶ ለማቋቋም ግብረ ሃይል ተቋቁሞ በተቀናጀ መንገድ እየተሰራ መሆኑንም ነው ያስታወቁት።

በአደጋው ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ ለሚገኙ ወገኖችም የምግብ፣ የቁሳቁስና የጤና አገልግሎት ድጋፍ ማድረግ መጀመሩን አቶ ጥላሁን ጠቁመዋል።

ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት የዓይነትና የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ የሚፈልጉ አካላት ከጋሞ ዞን አስተዳደር ጋር በመገናኘት ድጋፍ ማድረግ የሚችሉበት ምቹ ሁኔታም ተፈጥሯል ብለዋል።

መላው የኢትዮጵያ ህዝብም ለወገኑ ድጋፍ በማድረግ የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ ያቀረቡት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ የበልግ ዝናብ ቀጣይነት ያለው በመሆኑ የክልሉ ህዝብ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግም አሳስበዋል።


 

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት የአደጋ ሥጋት ምክር ቤት ለተጎጂ ወገኖች የሚውልና 2 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር ግምት ያለው የምግብና የአይነት ድጋፍ ማድረጉን የገለጹት ደግሞ የክልሉ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራርና ምግብ ዋስትና ኮሚሽነር ወገኔ ብዙነህ ናቸው።

ድጋፉ አስቸኳይ የምግብ አቅርቦትንና ሌሎች አስፈላጊ መሰረታዊ ቁሶችን ያካተተ መሆኑን ጠቁመው፣ በአደጋው የተጎዱትን መልሶ ለማቋቋም የተጀመረው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።


 

የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ደምስ አድማሱ(ዶ/ር) በበኩላቸው ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች አደጋው ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ ሰብዓዊና ቁሳዊ ድጋፍ እየቀረበ መሆኑንና ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም