ሀገር በቀል ዕውቀቶች ለማኅበራዊ ትስስር፣ ለዘላቂ የሰላምና ለኢኮኖሚ ግንባታ ያላቸውን ትልቅ ፋይዳ ይበልጥ ለማጎልበት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሀገር በቀል ዕውቀቶች ለማኅበራዊ ትስስር፣ ለዘላቂ የሰላምና ለኢኮኖሚ ግንባታ ያላቸውን ትልቅ ፋይዳ ይበልጥ ለማጎልበት እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 4/2018(ኢዜአ)፦ሀገር በቀል ዕውቀቶች ለማኅበራዊ ትስስር፣ ለዘላቂ ሰላም እና ለሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ ያላቸውን ትልቅ ፋይዳ ይበልጥ ለማጎልበት እየተሰራ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
ሀገር በቀል ዕውቀት አንድ ማኅበረሰብ ከአካባቢው ጋር ባለው የረጅም ጊዜ ግንኙነት የሚያዳብረው፣ በትውልድ ቅብብሎሽ የሚተላለፍና ለችግር መፍቻነት የሚያገለግል ጥበብ ነው።
በኢትዮጵያ ሀገር በቀል ዕውቀት እንደ "እድር" እና "እቁብ" ያሉ የኢኮኖሚ ዋስትናዎችን፣ እንደ "ሸንጎ" ያሉ ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓቶችን እንዲሁም በርካታ ዕውቅና ያገኙ ጥበቦችን ያካትታል።
እነዚህ ዕውቀቶች ለዘላቂ ልማት መሠረት ከመሆናቸውም በላይ ማኅበረሰቡ የራሱን ችግር በራሱ አቅምና ፍልስፍና እንዲፈታ ያስችሉታል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልማህዲ እንደገለጹት፤ ሚኒስቴሩ ሀገር በቀል ዕውቀቶችን በ10 ዋና ዋና ዘርፎች በመከፋፈል ሥራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡
እነዚህም የባህል መድኃኒቶችን፣ ባህላዊ የሽምግልና ሥርዓቶችን፣ የባህል ምግቦችንና ሌሎችንም የፈጠራ ጥበቦችን ጨምሮ በርካታ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
እነዚህ ዕውቀቶች ከማኅበራዊ ፋይዳቸው ባለፈ የሥራ ዕድል በመፍጠርና የገቢ ምንጭ በመሆን ለሀገር ኢኮኖሚ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሚኒስቴሩ ይህንን ታሳቢ ያደረገ የልማት ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባሕሎች አካዳሚ ምክትል ዳይሬክተር ደሳለኝ አምሳሉ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ሀገር በቀል ዕውቀቶች በተለይም ለሰላም ግንባታና ለግጭት መከላከል ያላቸውን ሚና አብራርተዋል።
ማኅበረሰቡ ለዘመናት ሲጠቀምባቸው የቆዩት የግጭት መፍቻ ሥርዓቶችና የዕፅዋት መድኃኒት ቅመማ ጥበቦች ይበልጥ ከዘመናዊው ሥርዓት ጋር ተሳስረው እንዲያድጉ ጥረት እየተደረገ ይገኛልም ብለዋል።
"ቡልኮ" የተሰኘ የሀገር በቀል ዕውቀቶች ጥናትና ምርምር መስራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ አብዱልፈታህ አብድላህ፤ እነዚህ ዕውቀቶች ለዛሬው ሕይወታችን መሠረት ናቸው ብለዋል።
ዕሴቶቹን ከዘመናዊው የትምህርት ሥርዓት ጋር በማቆራኘት ለትውልድ ለማሻገር እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።