ቀጥታ፡

የኢትዮጵያና የኖርዌይ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበ ነው- ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ

አዲስ አበባ፤መጋቢት 4/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያና የኖርዌይ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በተለያዩ መስኮች ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ገለጹ።

"የኢትዮጵያ እና ኖርዌይ የአስር ዓመታት የልብ ህክምና አጋርነት አቅምን በመገንባትና ሕይወትን በማዳን ሂደት" በሚል መሪ ሃሳብ ሲምፖዚየም በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በዚሁ ወቅት፥ የኢትዮጵያና የኖርዌይ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በጠንካራ ትብብር እና ወዳጅነት ስምንት አስርት ዓመታትን ተጠናክሮ መዝለቁን አስታውሰዋል።

በተለይም የልብ ህክምና አጋርነት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ጠንካራ ወዳጅነት የሚያረጋግጥ ትልቅ ማሳያ መሆኑን ገልፀዋል።

ይህ ትብብር ህይወትን ከማዳን ባለፈ ለታካሚዎች አዲስ ተስፋን የሰጠ መሆኑንም አስረድተዋል።

የዚህ አጋርነት ዋነኛው ተልዕኮ ህይወትን ማዳን ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ ዘላቂነቱ የሚረጋገጠው ግን በዕውቀትና በቴክኖሎጂ ሽግግር መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል።

በመሆኑም ይህ ትብብር በሀገር በቀል መፍትሄዎችና በላቀ የህክምና አገልግሎት ይበልጥ መጠናከር እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

ፕሬዝዳንቱ አክለውም የኢትዮጵያ መንግስት ከኖርዌይ ጋር በተለያዩ ዘርፎች የረጅም ዘመን ግንኙነት እንዳለው ጠቅሰው፤ ለዚህም በ1970ዎቹ ጀምሮ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ያለውን የአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስትቲዩትን ለአብነት አንስተዋል።

ኢንስቲትዩቱ በህክምና ምርምር ረገድ የልህቀት ማዕከል መሆን የቻለና በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ባለሙያዎችን በማፍራት ረገድ ግንባር ቀደም መሆኑን አስታውቀዋል።

በበሽታ መከላከል ላይ ያተኮረው የኢትዮጵያ የጤና ፖሊሲ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የጤና አገልግሎት ላይ ፈጣን ለውጥ እያመጣ እንደሚገኝ ፕሬዝዳንቱ ገልፀዋል።

የጤና መሰረተ ልማቶችን በማጠናከር አገልግሎቱን ተደራሽና ተመጣጣኝ ለማድረግ መንግስት በትጋት እየሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

ዩኒቨርሲቲዎች፣ ሆስፒታሎችና የመንግስት ተቋማት እንዲሁም አጋር አካላት በጋራ ሲሰሩ የህብረተሰቡን ህይወት መቀየር እንደሚቻል በተግባር መታየቱን አስረድተዋል።

በዚህ ረገድ የግል ዘርፉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

ህይወትን የሚታደጉና ተስፋን የሚመልሱ ተግባራት ላይ መሳተፍ ሁልጊዜም ትልቅ ደስታ መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዝዳንት ታዬ፤ ባለፉት አስርት ዓመታት ለተመዘገበው ስኬት መሰረት የሆነውን አጋርነት ማድነቅም አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል።

ለኢትዮጵያ እና ኖርዌይ የአስር ዓመታት የልብ ህክምና አጋርነት ስራ መሳካት መነሻ ለሆኑት የኖርዌይ የህክምና ባለሙያዎች፣ የሆስፒታሉ አመራሮችና ሰራተኞች ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም