በእናቶችና ሕፃናት ክብካቤ፣ ቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት አሰጣጥ እና ክትባት ላይ ትኩረት ያደረገ የዳሰሳ ጥናት ሊካሄድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በእናቶችና ሕፃናት ክብካቤ፣ ቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት አሰጣጥ እና ክትባት ላይ ትኩረት ያደረገ የዳሰሳ ጥናት ሊካሄድ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 4/2018(ኢዜአ)፦ጤና ሚኒስቴር በእናቶችና ሕፃናት ክብካቤ፣ ቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት አሰጣጥ እና ክትባት ላይ ትኩረት ያደረገ የዳሰሳ ጥናት ሊያካሄድ መሆኑን ገለጸ፡፡
ጤና ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የቀረጸው ሀገር አቀፍ የጥናት ፕሮጀክት የመስክ ሥራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በዛሬው ዕለት ተካሂዷል።
የዳሰሳ ጥናቱ በአገር አቀፍ ደረጃ በእናቶችና ሕፃናት ጤና አጠባበቅ ዙሪያ ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑ የተገለጸ ሲሆን የመስክ ሥራ መጀመሩም ይፋ ተደርጓል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ድጉማ እንደገለጹት፤ መንግስት መረጃን መሠረት ያደረገ የውሳኔ አሰጣጥ ሥርዓትን ለመገንባት በሰጠው ትኩረት በእናቶችና ሕፃናት ላይ ይደርስ የነበረውን የሞት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ ተችሏል።
ይህ ውጤት ሊመዘገብ የቻለውም ከለውጡ ወዲህ የጤና ተቋማትን በማስፋፋት፣ ግብዓቶችን በማሟላት እና እናቶች በቅድመና ድህረ ወሊድ ወቅት የሕክምና ክትትል እንዲያደርጉ ግንዛቤ በመፈጠሩ መሆኑን ገልጸዋል።
አሁን የሚካሄደው የዳሰሳ ጥናት በተለይም በቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ተደራሽነት፣ በእናቶችና ሕፃናት የጤና ክብካቤ ጥራት እንዲሁም በክትባት ሽፋን ዙሪያ ያለውን ተጨባጭ መረጃ ለማወቅና ለቀጣይ የፖሊሲ ውሳኔዎች እንደ ግብዓት ለመጠቀም ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አስረድተዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት ዲን ዶክተር ሙሉጌታ ታምሬ በበኩላቸው፤ ጥናቱ ሁሉንም የአገሪቱ ክልሎች የሚያካትት መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህ የኢትዮጵያ አፈጻጸም ክትትል ትግበራ ጥናት ለአምስት ዓመታት የሚቆይ ሲሆን በአገር አቀፍ ደረጃ የተደራጀ መረጃን በማቅረብ የጤናውን ዘርፍ ውጤታማነት ለማረጋገጥና በዘርፉ የልህቀት ማዕከል ለመገንባት ያግዛል ብለዋል።
በዚሁ የምርምር ሥራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የጤና የሥራ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን ጥናቱ የሚሰበስባቸው መረጃዎች የጤና አገልግሎት ተጠቃሚነትን ይበልጥ ለማሳደግ መሠረት እንደሚሆኑ ተገልጿል፡፡